Tuesday, July 23, 2013

መልክአ ስብሐት - የስብሐት መልክ?

መልክአ ስብሐት - የስብሐት መልክ? [Controversy over the title of new book about Sebhat Gebre-Egzehabher]

በ8-11-2005 ዓ.ም. በጣይቱ ሆቴል በደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ሕይዎትና ፍልስፍናዎቹ ዙሪያ “መልክአ ስብሐት” የተሰኘ መጽሐፍ መመረቁ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዘመን ላለን ማንነታችንን እየረሳን ቋንቋና መገለጫ እንደሌለን ሁሉ ከልጆቻችን ስሞች አንሥቶ እስከ ድርጅቶቻችን ድረስ የባዕዳን ቋንቋና መገለጫ የሆኑ ሥያሜዎች በመስጠት ለተለከፍነውና ሥልጣኔና ዘመናዊነት መስሎ ለሚታየን አላዋቂዎችና ምርኮኞች የዚህ መጽሐፍ ርእስ በአርዓያነት ወይም እንደጥሩ ምሳሌ ሊወሰድ የሚገባው ነው፡፡ ነገር ግን መጽሐፉ በትክክል የስብሐት ገ/እግዚአብሔርን ማንነት እንድናውቀው በሚያስችል ሁሌታ የሙሉ ሰብእናውን ገጽታ አሳይቷል ወይ የሚለው ጥያቄ ሌላ ነገር ሆኖ ለመጽሐፉ በተሰጠው ርእስ ላይ ግን ጥቂት ነገር ለማለት እፈልጋለሁ ፡፡ ለመጽሐፉ የተሰጠው ርእስ መልክአ ስብሐት ተብሏል፡፡ መልክአ የሚለው ቃል ግእዝ ነው ትርጉሙም የ----መልክ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ የመጽሐፉ አዘጋጅ መልክአ ስብሐት ሲሉ የሠየሙትን መጽሐፍ ስንተረጉመው የስብሐት መልክ ማለት ይሆናል፡፡ መልክአ እከሌ ፣ መልክአ እንደዚህ የሚለው ቃል እስከ አሁን አገልግሎት ላይ የዋለው በግእዝ የጸሎት መጻሕፍት ሆኖ ውዳሴ ምስጋናና የምልጃ ጸሎት ሊቀርብለት ለተፈለገው ከእግዚአብሔር(ከመድኃኔዓለም ክርስቶስ) አንሥቶ አስከ ቅዱሳን ላሉት ነበር፡፡ በእርግጥ ግእዝ እንደማንኛውም ቋንቋ ቋንቋ ነውና ርእሱ አሁን ለስብሐት ገ/እግዚአብሔር መሰጠቱ ብቻውን በራሱ ምንም ችግር የለውም፡፡ ችግር የሚሆነው ርእሱና ሊባል የተፈለገው ነገር ተስማምቷል ወይ ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ ነው ፡፡ በግእዝ የመልክ የጸሎት መጻሕፍት ድርሰቶች ላይ የሚገለጸው ሐሳብ ቃሉ እንደሚያመለክተው ማለትም ያ መልክ የተደረሰለት ቅዱስ ለምሳሌ የክርስቶስ ኢየሱስን ብንወስድ መልኩን ወይም ውበቱን ከገጹ ጀምሮ ሰላም ለዐይኖችህ፣ ለአፍንጫህ፣ ለከናፍርህ፣ ለጥርሶችህ እያለ ከራስ ጸጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ ያሉትን የሰውነት ክፍሎቹን ሁሉ ውበታቸውን ማድነቅ፣ ማወደስ፣ ክብራቸውን መግለጽ፣ በእያንዳንዱ የውዳሴ አንቀጾችም የምሕረት ምልጃ ጸሎት ማቅረብ፣ ታድጎቱን፣ ማዳኑን፣ ጥበቃውን መማጸን ማለት ነው፡፡ እንግዲህ የመልክ መጽሐፍ ይዘቱ ወይም አቋሙ ይሄንን ይመስላል፡፡ ከዚህ አንፃር የመልክአ ስብሕት መጽሕፍ አዘጋጆች ሊሉ የፈለጉት ወይም ያሉትና የመልክ መጽሐፍ ይዘት ፈጽሞ የማይስማሙ ያለዕውቀት ወይም ሙሉ ግንዛቤ ሳይያዝ ለመጽሐፉ ሥያሜውን እንደሰጡ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡ የሐሳባቸው መነሻ ጥሩ ሆኖ ሳለ ሊሰጡ የፈለጉት ወይም የሰጡት ሥያሜ ሊሉ ከፈለጉት ወይም ካሉት ጋር መስማማቱን ባለማረጋገጣቸው ግን ስሕተቱ ሊፈጠር ቻለ፡፡ ከመጽሐፉ ይዘት አንጻር ለመጽሐፉ የግእዝ ሥያሜ እናውጣለት ቢባል ለመጽሐፉ የሚስማማው ሥያሜ ግብረ ስብሐት የሚለው ሥያሜ ነበር ተስማሚው፡፡ ስብሐት ጠላት ኖሮበት ሲጋደል ኖሮ ያለፈ ቢሆንና ያንን ተጋድሎ የሚያወሳ የሚዘክር መጽሐፍ ቢጻፍ ለዚህ መጽሐፍ ተስማሚ የሚሆነው ሥያሜ ደግሞ ገድለ ሥብሐት የሚለው ሥያሜ ነበር፡፡ በመሆኑም የመጽሐፉ አዘጋጆች ገጸ-ባሕርያቱን እየቀያየሩ በዚያው ሥያሜ ስለ ገጸ-ባሕርያቱ አስተሳሰብ ሰብእናና ሕይወት በተከታታይ የመጻፍ ዓላማ አላቸውና ለተሳሳተው ሥያሜ ማስተካከያ አድርገው ይቀጥሉበት ዘንድ ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ምልካም ሥራ ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው amsalugkidan@gmail.com

source.... http://sodere.com

No comments:

Post a Comment