Thursday, July 25, 2013

የደቡብ ሱዳን ሚኒስትሮች እገዳ

የደቡብ ሱዳን ሚኒስትሮች እገዳ

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የሃገሪቱን ካቢኔ ካገዱ በኋላ ዋና ዋና የመንግሥት ተቋማት አካባቢ ጥበቃው ተጠናክሯል ። ከፕሬዝዳንቱ እርምጃ በኋላ ህዝቡ እንዲረጋጋ በራድዮ ጥሪ ተላልፏል ።
ከሥልጣን ከተወገዱት ባለሥልጣናት መካከል ተሰሚነት ያላቸው ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቼርና የገዥው የሱዳን ህዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ በእንግሊዘኛው ምህፃር SPLM ዋና ፀሃፊ ፓጋን አሙም ይገኙበታል ። የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር 29 ሚኒስትሮችንና ምክትሎቻቸውን በሙሉ ነው ከሥልጣን ያገዱት ። ትናንት ከሥራቸው ከታገዱት ባለሥልጣናት መካከል 17 የፖሊስ ሃላፊዎችም ይገኙበታል ። እስከታገደቡት ጊዜ ድረስ የማስታወቂያ ሚኒስትርና የመንግሥት ቃል አቀባይ የነበሩት ባርናባ ማርያል ቤንያሚን ትንንት ማምሻውን ዜጎች እንዲረጋጉና የተለመደውን ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ ተማፅነዋል ።
ሳልቫ ኪር
ይሁንና እገዳው ነፃነቷን ከተቀዳጀት 2 ዓመትት ብቻ ባስቆጠረችውና ለዓመታት ከተካሄደ ጦርነት ገና በማገገም ላይ ባለችው ደቡብ ሱዳን አለመረጋጋትን ያስከትላል የሚል ስጋት አሳድሯል ። የአሁኑ የባለሥልጣናት እገዳ እንደ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ድንገተኛ የሚባል እርምጃ አይደለም ። በሱዳን የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ ሃላፊ ፔተር ሹማን ሳላቫ ኪር ቀደም ባሉት ጊዜያትም አንዳንድ ምልክቶችን አሳይተው ነበር ይላሉ ። « ከጀመረ ጥቂት ቆየት ብሏል ። SPLM ውስጥ ትግል አለ ። ትግሉም ሥልጣን ለመያዝ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ስልትና ይዘቱንም ለመቆጣጠር ጭምር ነው ። እንደሚመስለኝ ሳልቫ ኪር የዩኒቲ ስቴት አገረ ገዥን ሲያባርሩና ሁለት ሚኒስትሮችን በሙስና ከሰው ሲያሰናብቱ መጠነኛ ምልክት ማየት ጀምረን ነበር ።አሁን ካቢኔያቸውን የማባረር እርምጃ በመውሰዳቸውና የሚኒስትሮቻቸውንም ቁጥር መቀነሳቸው አያስደንቀኝም ። አሁን የሚያደርጉት ከፍተኛውን ሥልጣን ማን ይይዛል ከሚለውም ጨዋታ በላይ ነው »

ሪክ ማቼር

አሁን ከተባረሩት ባለሥልጣናት ውስጥ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቼር ና የSPLM ዋና ፀሃፊ ፓጋን አሙም አሉ ። እነዚህ ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ደግሞ ፍሬድሪሽ ኤበርት የተባለው የጀርመን የጥናት ተቋም ሃላፊ ፍሎርያና ዴን ለዶቼቬለ እንደተናገሩት የሳልቪር ተቀናቃኞች ነበሩ ።
« ሪክ ማቼርና ፓጋን አሙም ሁለቱም ጠንካራ ባህርይ ያላቸው ሲሆኑ በፓርቲያቸው የስልጣን ተዋረድም ሆነ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ አላቸው ። ሁለቱም በአሁኑ ፕሬዝዳንቱ የመንግሥት አስተዳደር ላይ ጠንካራ ይነቅፉ ነበር ። በግልም የፖለቲካ ሥልጣናቸውም የመውረስ ጉጉት እንደነበራቸው በግልፅ አሳይተዋል ። »
ሳልቫ ኪር አሁን የወሰዱት እርምጃ በደቡብ ሱዳን አደጋ ማስከተሉ እንደማይቀር ያሰጋል ። ፔተር ሹማን አደጋውን ከጎሳ ግጭት ጋር ነው የሚያያዙት ።

ፓጋን አሙም

« አደጋው እንዳለነው አሁን የጎሳ ጉዳይ እንደገና ወደ ላይ እየመጣ ፣ አስከፊ መልኩንም እያሳየ መሆኑን እንመለከታለም ። የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ይህን የጎሳ ጉዳይ ለዓላማቸው ማሳኪያነት ይጠቀሙበታል ብዬ ተስፋ አላደርግም ። ሪያክ ማቻር የጎሳ ፖለቲካን መሣሪያ ያደርጋሉ ብዮ አላምንም ። ከርሳቸው በታች ያሉ ሰዎች ግን ምናልባትም ሊጠቀሙበት ይችላሉ ።»
ፕሬዝዳንት ኪር ህገ መንግሥቱ በሰጣቸው ሥልጣን መሰረት ካቢኔያቸውን መቀየር ይችላሉ ። ሆኖም የፓርቲያቸውን ዋና ፀሃፊ እንዴት እንዳነሱ ግን ግልፅ አይደለም ይላሉ ፔተር ሹማን ። የፍሬድሬሽ ኤበርቱ ሃላፊ ፍሎርያን ዴን እንዳሉት ደግሞ አሁን ከሥልጣን የታገዱት የደቡብ ሱዳን ባለሥልጣናት በሙሉ ለረጅም ጊዜ ተባረው ይቆያሉ ማለት አይደለም ። በሌላ በኩል ደግሞ፣ ለማቼርና ለአሙም ታማኝ ናቸው ከሚባሉት በስተቀር በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ እንደገና ልንሾም እንችላለን ብለው የሚጠብቁ በርካታ ሚንስትሮች እንዳሉ ነው ዴነ ያስታወቁት።

ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ

germen radio

No comments:

Post a Comment