Thursday, July 11, 2013

ሰር ቻርሊ ቻፕሊን (የታላቁ ዲክታተር ንግግር)

የቻርሌ ቻፕሊን  የህይወ ትታሪክ  ባጭሩ
ታላቁ የድምጽ አልባ ፊልሞች (silent movies) ተዋናይ ደራሲ አዘጋጅና በቧልታይ መልክ ሂሶችን፤ ትችቶችን፤ ሰብአዊነትን፤ ልማትን፤ እድገትን በማስተማር ረገድ ከፍተኛ ቦታ የተሰጠው ባለሙያ ሰር ቻርሊ ቻፕሊን በኤፕሪል 16 1889 በእንግሊዝ ሃገር በለንደን ተወለደ፡፡ ቻርሊ ቻፕሊን ወደ ትልቁ የፊልም ስራ ተወዳጅነቱ ከመዝለቁ በፊት በሕጻንነቱ የዳንስ ቡድን ውስጥ ሲሰራ ነበር፡፡ በስተኋላ ላይ የታወቀበት የተከታታይ የፊልም መጠሪያው  ‹‹ቻርሊ ዘ ተራምፕ›› ሲሆን ድምጽ አልባ ፊልም ብቻ ይቀርብበት በነበረው ዘመን፤ ታሪኩን በእንቅስቃሴ ብቻ በማቅረብና አካሄዱንም ፈጥን በማድረግ ለባሕሪው በፈጠረለት ይዘትና በሚያቀርባቸው ታሪኮች ተወዳጅነት ከማትረፉም ባሻገር ለድምጽ አልባው ፊልም መወደድና መዳበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በሂደትም የተዋጣለት ባለሙያ በመሆንና ወደ አዘጋጅነት በመሰማራት ጥንድ ሙያውን ተዋናይም አዘጋጅም ሆኖ በመስራት እስካሁን ድረስ ታላቅ በመባል ከሚታወቁት የፊልም ስቱዲዎች አንዱ የሆነውን ዩናይትድ አርቲስትስ ኮኦፖሬሽንን በማቋቋም ግንባር ቀደም ሆነ፡፡ በዚህም ስቱድዮ (City Lights and Modern Times) እንደ ‹‹የከተማ መብራቶችና ዘመናዊነት››  ያሉትን ፊልም ሰራ፡፡

በፈጠረው የግሉ ባሕሪው መገለጫ በሆነው ከዘራው፤ በክብ ጠፍጣፋ ኮፍያው፤ቻርሊ ቻፕሊን ማንም ሰው ሊያደርገው በማይሆንለት መልክ የሙያው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረስ የሙያውን አምባም በዚያው መልኩ ለማሳደግ የበቃ አርቲስት ነበር፡፡ አስተዳደጉን በተመለከተ ያንን ሁኔታ አልፎ ለዚህ መድረሱ በጣሙን አስገራሚ ነው፡፡ አባቱ የመጠጥ ሱስ ልክፍተኛ ነበርና ቻርሊን ታላቅ ወንድሙን እናቱን ቻርሊ እንደተወለደ ጥሏቸው ጠፋ፡፡ይህም ቻርሊንና ወንድሙን ለማሳደግ ሃላፊነቱን በሙዚቃ አዳራሽ ውስጥ ሊሊ ሃርሊ በሚል ስም በዘማሪነት የምትሰራው እናቱ መሸከም ነበረባት፡፡

የቻፕሊን እናት ወደ ኋላ ላይ በአእምሮ መታወክ ታማ ወደ ሆስፒታል ብትገባም እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን እርዳታዋን አላስተጓጎለችም፡፡ በአንድ ወቅት እናትዬዋ በመድረክ ላይ ዜማዎቿን በማቅረብ ላይ ሳለች በድንገት ድምጽዋ በመጥፋቱ ሳቢያ የመድረክ አስተጋባሪው አልፎ አልፎ ሲዘፍን ይሰማው የነበረውን ህጻኑን የአምስት ዓመት ልጅ ቻርሊ ቻፕሊንን እናቱን ተክቶ እንዲያዜም ወደ መድረክ ገፍቶ አስገባው፡፡ ቻፕሊንም በማይታመን ሁኔታ  በእድሜው ድጋፍ ቀልድም በመጨማመር ሲዘፍን፤ ሲንቀሳቀስ፤ በስተመጨረሻውም የእናቱን ድምጽ መሻከርና መጥፋት በማስመሰል ተመልካቹን አስፈነደቀ፡፡ ይህ ዕለት ግን የእናቱ የሙያ ማክተሚያ ሆነ፡፡ድምጽዋም ባለመመለሱና መስራት ባለመቻሏ፤ ገንዘቡም እያለቀ በመሄዱ፤ ቻርሊና ወንድሙ ኑሮን ለማሸነፍ በአስቸጋሪ  የለንደን ሥራ ቦታዎች መቀጠር ነበረባቸው፡፡

ቀደምት የሙያ ሁኔታ

እናቱ ለመድረክ የነበራትንና ፍቅርና አክብሮት በማንገብ፤ቻፕሊን ሕይወቱን ወደ ጥበብ ለማስገባትና መኖሪያው ለማድረግ ወሳኝ አቋም ነበረው:: በዚህም መሰረት እናቱ ፈጥራለት በነበረው ግንኙነት ሄዶ፤ ‹‹ስምንቱ የላንክሻየር ጉብሎች›› የሚባለው የዳንስ ቡድን ውስጥ በአባልነት ተቀላቀለ፡ችግሩን መቅረፊያ ሆነለት፡፡ ‹‹ እኔ በተለያየ ስራ ዘርፍ ውስጥ፤ ጋዜጣ አዳይ፤ ቀለም ቀቢ፤ የዲክተር ተላላኪ፤ የአሻንጉሊት ፋብሪካ ሰራተኛ›› በመሆን ብሰራም ያን የተዋናይነት ሕልሜን ግን ለአፍታም ዘንግቼው አላውቅም፡፡ ‹‹በየስራው ቦታ የእረፍት ቀኔ ጫማዬን ወልውዬ፤ ልብሶቼን አጸዳድቼ፤ ጸአዳ ሸሚዜን ከነክራባቱ በመደረብ በየቴአትር ቤቶቹ ሥራ ጥየቃ ማንኳኳቴንን በኤጀንሲ ቢሮ  ደጅ መጥናቴን አላቋረጥኩም›› ይል ነበር ቻፕሊን::

አንድ ቀን ሌሎች ከመድረክ ጋር ተጓዳኝ የሆኑ ስራዎች አገኘ፡፡ ቻፕሊን በሼርሎክ ሆልምስ የቴአትር ዝግጅት ውስጥ የተላላኪውን ቦታ በመጫወት ለመድረክ በቃ፡፡ ከዚያም ካቲ ኮርት ሰርከስ የተባለው ቡድን አባል ሆኖ በተዋናይነት መዘዋወር ጀመረ፡፡ ለጥቆ በ1908 ከፍሬድ ካኖ ፓንቶማይም (ቃል አልባ ተውኔት) ጋር በመጓደን  ቻፕሊን ‹‹አንድ ምሽት በእንግሊዝ የሙዚቃ አዳራሽ›› በተባለው ዝግጅት በተሰጠው የሰካራም ባህሪ ከቡድኑ አባላት ነጥሮ በመውጣት ታዋቂ መሆን ጀመረ፡፡ ከዚህ ቡድን ጋር ባደረገው ጉዞ አሜሪካን ለመጀመርያ ጊዜ ለማየት በቅቶ በዚያም አጋጣሚ ማክ ሴኔት የተባለ የፊልም አምራች ባለሃብት አይን ገብቶ፤ በሳምንት 150 ዶላር ኮንትራት ፈረመ፡፡
በዚህ ጊዜ ነው ቻፕሊን የፊልም ሙያ በር በሰፊው የተከፈተለት፡፡ ወዲያውም እራሱን በበለጠ ለማስተዋወቅና በራሱ መንገድ፤ ለዘመናት ዘልቆ እስካሁንም ድረስ  የዘለቀውን ባሕሪ በመፍጠር የብቻ ተውኔቱን ለዓለም ያበረከተው፡፡

ቻርሊ ቻፕሊን የሚያቀርባቸው ፊልሞች በአብዛኛው በማሳሳቅ የሕብረተሰቡን ችግር የሚያሳዩ፤ ሰብአዊነትን የሚያስተምሩ፤ ግፍን የሚቃወሙ፤ ለሕዝብ አጋርነትን የሚሰብኩ ስለነበሩና ለማንኛውም ተመልካች ለትልቁም፤ ለትንሹም ባለእድሜ የሚሆኑ ስራዎች ናቸው፡፡ በተደጋጋሚ በኮሚኒስትነት በመጠርጠር ክትትልና ምርመራም ቢደረግበትም ሃሰት የሆነ ጉዳይ በመሆኑና ‹‹ለሰው ልጅ ደህንነት መቆም በራሱ ኮሚኒስት አያሰኝም፤ ይህም መብት በአሜሪካው ሕገመንግስት የተቀመጠ ድንጋጌ ነው›› በማለት በአጋጣሚው ሁሉ እያስረዳ ኖሮ፤ በሙያው ተከብሮ፤ ዓላማውን ሳይስትና ሙያውንና እምነቱን ለገንዘብና ለጥቅማጥቅም ሳይለውጥ የኖረ ሕዝባዊ የጥበብ ባለሙያነቱ ስለታመነበት በተወለደበት እንግሊዝ ሃገር የ‹‹ሰር››ነት ታላቅ ክብር የተቀዳጀ ባለሙያ ለመባልና በጠቅላላው የዓለም ላይ ሕዝብ ፍቅር ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ያተረፈ፤ ዘመን የማይሽራቸውን ስራዎቹን ትቶ ያለፈ ባለሙያ ነው፡፡

የታላቁ ዲክታተር ንግግር (The Great Dictator)

በጣም አዝናለሁ፤ እኔ ንጉሠ ነገሥት መሆን አልፈልግም፡፤ ያ የኔ ሙያ አይደለም፡፡ እኔ ማንንም ተዋግቼ በማሸነፍ መግዛት አልፈልግም፡፡ቢቻለኝ፤ሁሉንም መርዳት እመርጣለሁ፡ – ይሁዲውን- አሕዛብን-ጥቁሩን- ነጩንም፡፡ ሁላችንም ለመረዳዳት እንፈልጋለን፡፡ ሰብአዊ ፍጡራን እንደዚያ ናቸው፡፡ እያንዳንዳችን በእያንዳንዳችን ሰቆቃ ሳይሆን በያንዳንዳችን ደስታ መኖር እንፈልጋለን፡፡ አንዳችን ሌላችንን መጥላትና መናቅ አንፈልግም፡፡ በዚህ ዓለም እኮ ለሁሉም ቦታ አለ፡፡ መልካሟ መሬት ደግሞ የተትረፈረፈ ሃብት ስላላት ለሁሉም ታዳርሳለች፡፡ የሕይወታችን መንገድ ነጻና ውብ ሊሆን ይችላል፤ ግና መንገዱ ጠፍቶናል፡፡
ንፍገት የሰዎችን ሕሊና አብልዞታል፤ ዓለምን በጥላቻ ሰንክሎታል፤ በዝይ ስውር መንገድ ወደ መከራ ስቃይና ደም መፋሰስ መርቶናል፡፡ ፍጥነት ብናዳብርም እራሳችንን አስረናል፡፡ በገፍ የሚያመርተው ፋብሪካ የበለጠ ፈላጊዎች አድርጎናል፡፡ ዕውቀታችን ተጠራጣሪ አድርጎናል፡፡ ብልጥነታችን ኢሰብአዊና መጥፎነት ነው፡፡ ብዙ እያሰብን አናሳ ስሜት ተፈጥሮብናል፡፡ ከማምረቻ መሳርያ ይልቅ፤ ፍጡራን፤ ሰብአዊዎች ያስፈልጉናል፡፡ ከብልጠት ይልቅ፤ ደግነትን እና ርህራሄ ያስፈልገናል፡፡ከነዚህ ሁኔታዎች ውጪ ሕይወት ቁጡ ትሆንና ሁሉም ይጠፋል…….
አውሮፕላንና ሬዲዮ አቀራርቦናል፡፡ የነዚህ ፈጠራ ተፈጥሮ የሰዎችን መልካምነት፤ ለዓለም አቀፍ ወንድማማችነት በመጣራት ላይ ነው- ለሁላችንም በአንድ ለመተሳሰር- አንድ ለመሆን ብቃት፡፡አሁን እንኳን ይህ አባባሌ በዓለም ላሉ ተስፋ የቆረጡ ሚሊዮኖች ወንዶችና ሴቶች፤ ለታዳጊ ሕጻናት፤ ሰብአዊ ፍጡራንን በስርአታቸው ማነቆ ለሚያስሩ፤ ለሚያሰቃዩ፤ መልካም ሰዎችን በወህኒ ለሚያጉሩም ጨቋኞች ይደርሳል፡፡
ለሚያዳምጡኝ፤ እባካችሁ ተስፋ አትቁረጡ እላለሁ፡፡ አሁን በላያችን ላይ የተከመረብን ችጋርና ሰቆቃ፤የንፉግነታችን፤ የሰብአዊ ፍጡርን እድገት ማየትና መቀበል የሚይፈቅዱ ሰዎች መጥፊያ ነው- የሰዎች ጥላቻ ያልፋል፤ እናም ዲክታተሮች ይሞታሉ- ያም ከሕዝብ የሰረቁት ሃይል ወደ ባለቤቱ ሕዝብ ይመለሳል፡፡ ሰዎች ለሞት እስከተዳረጉ ድረስ፤ ነጻነት፤ መብት አይረግብም………..
ሕዝባዊ ወታደሮች!  እራሳችሁን ማሰብ ለተሳናቸው አውሬዎች አታስገዙ- ለሚንቋችሁ – ለባርነት ለሚዳርጓችሁ – ሕይወታችሁን ለሚያጠወልጉት – የምታደርጉትን- ምን ማሰብ እንዳለባችሁ እና ምን መከወን እንዳለባችሁ ለሚነግሯችሁ – የድርጊት ቅደም ተከተል ለሚያወጡላችሁ – ለሚያስርቧችሁ- እንደ መንጋ አውሬ ለሚቆጥሯችሁ – እንደ መድፍ ተሸካሚዎች ለሚያይዋችሁ ለእነዚህ ከተፈጥሮ ሕግጋት ውጪ ለሆኑ ሰዎች እራሳችሁን አትስጡ – በመሳርያ የሚነዱ የመሳርያ ፍብረካዎች – በመሳርያ የተፈበረኩ በመሳርያ ድጋፍ የሚያስቡ- ልባቸው የተፈበረከ፡፡ እናንተ እኮ የመሳርያ ውጤቶች አይደላችሁም! መንጋ ከብቶችም አይደላችሁም! እናንተ ሰብአዊ ፍጡራን ናችሁ! በልባችሁ የሰብአዊ ፍጡር ፍቅር ተቀርጾባችኋል! ጥላቻ አታውቁም! ፍቅር የተሳናቸው ናቸው ጥላቻ የነገሰባቸው- ፍቅር የተነፈጉና ከተፈጥሮ ሕግጋት ውጪ የሆኑ አገልጋይ ወታደሮች! ምርጫችሁ ለባርነት ከመዋጋት ለነጻነት መዋጋትን  ይሁን!
በሉቃስ ወንጌል 17ኛው ምዕራፍ ላይ፤ ‹‹የአግዚአብሔር መንግሥት በሰዎች ውስጥ ነው››- ተብሏል-  በአንድ ሰው አይደለም- በተቧደኑ ሰዎችም አይደለም – ይልቅስ በሁሉም ሰዎች ውስጥ እንጂ – በአንተ – አንተ – - ሕዘቡ – የሥልጣን ባለቤቶች ናችሁ – መሳርያ የመፍጠር ሃይሎች፡፡ ደስታን ለመፍጠር ችሎታና ሃይሉ ያላችሁ – አንተ- ሕዝቡ – ይህን ሕይወት ነጻና ውብ ለማድረግ፡፡ ይህን ሕይወት በውበት የተሞላ ጀብዱ ለማድረግ ችሎታው አላችሁ፡፡

እንግዲያውስ – በዴሞክራሲ ስም- ያን ሃይል ጥቅም ላይ እናውለው- ሁላችንም ሕብረት ፈጥረን አንድ እንሁን – ለአዲስ ዓለም እንሟገት – ለመልክም ዓለም፤ ለሰዎች የመስራት እድል ለሚያመቻቸው – ለወጣቱ የነግህ ተስፋ ለሚሰጠውና ለዕድሜ ባለጸጎች ዋስትና ለሚያረጋግጠው፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ቃል ኪዳን አውሬዎችና ጨካኞች ወደ ስልጣን ወጥተዋል፡፡ ነገር ግን ቀላማጆችና ውሸታሞች ናቸው፡፡ የገቡትን ቃል ኪዳን ያፈርሳሉ፡፡መቼም ቢሆን ለቃላቸው አይገዙም፡፡

ዲክታተሮች እራሳቸውን ነጻ በማውጣት ብዙሃኑን ሕዝብ ለባርነት ይዳርጋሉ! ዓለምን ነጻ ለማድረግ እንዋጋ – ንፉግነትን፤ ጥላቻን፤ አለመቻቻልን ለማስወግድ ብሐራዊ መሰናክሎችን እናጣፋ፡፡ ምክንያታዊ ለሆነው ዓለም ዘብ በመቆም – የሳይንስ እድገትና ብልጽግና ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ደስታ እንዲሆኑ እንጣር፡፡ ወታደሮች! በዴሞክራሲ ስም ሁላችንም ሕብረት ፈጥረን አንድ እንሁን!

source...ecadforum.com

No comments:

Post a Comment