ኤሎሄ! ቅዱስ! ኤልሻዳይ! አዶናይ! ያህዌ! ጸባዖት! ኢየሱስ! ክርስቶስ! አማኑኤል! በአብ
በወልድ በመንፈስቅዱስ ሥም! አሜን! አቤቱ አባት ሆይ ከእኛ ወገን ለአንተ እናት ሆናህ በእሷ በኩል በሥጋ ትዛመደን በመረጥካትና ቅድስት፣ ንፅህትና ዘላለማዊት ድንግል በሆነች እናትህ ድንግል
ማሪያም ሥማ ማስተዋልን ትሰጠኝ ዘንድ እለምንሀለሁ! አሜን!
ባለፈው ጽሑፌ ማይክሮ ችፕስ 1 (ትውልድን የሚያመክን የትምህርት ሂደት፡ ) ለመጠቆም ሞከሪያለሁ፡፡ በዚህ
ጽሑፍ ሌሎች ማይከሮ ችፕስ አይነቶችን ልጠቁም ወደድሁ፡፡ የባለፈውን ላላነበባችሁ ማይክሮ ችፕስ የሚለውን ነገር እኔ በራሴ የፈጠርኩት
ሳይሆን በአንድ ታዋቂ ሰው ግብዣ ከአንድ የሚስጢር መጽሐፍ ያነበብኩት አስገራሚ አንቀፅ ነው፡፡ መልዕክቱም "የኢትዮጵያውያንን
አእምሮ ማይክሮ ችፕስ በመጠቀም እናፈዘዋለን ከዚያም የአሪቱን ሀብትም አገርቱንም እንቆጣጠራለን" የሚል ነው፡፡ ነገሩ እኔ
በማስባቸው ነገሮች ተረጎምኩት እንጂ ጉዳዩ ከዚያም በላይ ይሆናል፡፡ በቀጥታስ እውንም ማይከሮ ችፕስን ወደሰውነታችን አስገብተውብን
ከሆነ፡፡ ለማንኛውም እኔ ቀጥተኛም ባይሆኑ ስልታዊ ማይክሮ ችፕሶችን ልቀጥል
ማይክሮ ችፕስ 2 አስተዳደር፣ ባህልንና ሀይማኖትን መበረዝ፡ ድህነት ክፉ ነው፡፡ የራስ የሆነውን ጥሩንና
መጥፎውን ለይቶ ለማወቅ እንኳን እድል እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ ድህነታችን በትክክልም ባለመስራታችንና ይልቁንም ለዘመናት ጥሩ እድል
ሊፈጥሩልን የሚችሉትን ሀይማኖታዊና ማሕበረሰባዊ በጎ እሴቶችን ለብልፅግናና ለጥበብ አለመጠቀማችን እንደሆነ ሳንረዳ የእኛ የሆነው
ሁሉ የድህነታችን ምክነያት አንደሆነ ስለምናስብ ሐይማኖታዊውንም በጎ የሆኑ ማህበረሰባዊ እሴቶችንም ሁሉ በጅምላ ኮነንናቸው፡፡ ያደጉ
አገራት ከእኛ በሀይማኖትም በባህላዊ እሴትም በሁሉም ከእኛ እንደሚበልጡና የእነሱ የሆነው ሁሉ ትክክል እንደሆነ ተቀበልን፡፡ የሚያሳዝነው
መቼም ቢሆን የእነሱ የእኛ አይሆንም ያው ባሪያ የጌታውን ሊቀበል የግድ ካልሆነ በቀር፡፡ እነሱም የእነሱን ስንከተል የእኛ አያደርጉትም
ይልቁንም የእነሱን የእኛ እንዲሆን ስላደረጉና በእነሱ ስር ስለወደቅን የበታችነታችንን እንድናምን መረጃ ያደርጉታል እንጂ፡፡ ዛሬም
ድረስ እነዚያን ግፍ የሰሩባቸውን የቅኝ ግዛት ዘመናት ቅኝ የገዙባቸውን አገራት እየጠቀሱልን በኩራት ነው የሚያወሩን፡፡ ባሮቹም
ቅኝ የገዟቸውን አገራት አንደ አሳዳሪያቸው ነው አሁንም የሚያዩአቸው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት አለመውደቋን በኩራት ለመናገር
እኛ ዛሬ ድፍረት የለንም፡፡ ይልቁንም አለመገዛታችንን የኋላቀርነታችን ምክነያት የምናደርገው ብዙዎች ነን፡፡ ለዛም ነው ዛሬ የእኛው
የሆነውን እየተጠየፍንው የሌሎችን የምንናፍቀው፡፡ ጉዳዩ በጣም ብዙ ነው፡፡ ግን ለማሳያ ያህል እስኪ ሀይማኖትንና ቋንቋን ለማየት
እንሞክር፡፡
ሀይማኖት፡- ኢትዮጵያ ለክርስትናውም ሆነ ለእስልምናው ቀዳሚ አገር መሆኗን ብዙ ዜጎቿ ዛሬ አንረዳም፡፡ ብንረዳም
እንዲሆን ባለመፈለጋችን እንክደዋለን፡፡ ብዙዎቻችን ክርስትናው ከፈረንጅ እስልምናው ከአረብ ካለመጣ አይዋጥልንም፡፡ ፈረንጆቹም ክርስትናው
አረቦቹም እስልምናው ከእንሱ በፊት ኢትዮጵያ እንደሆነ አሳምረው ያውቁታል፡፡ እውነታው ያ ስለሆነ መቀበላቸው ግድ ሆኖባቸው እንጂ
የእኛ ከእነሱ ባይቀድም ይወዱ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው እኛ በእምነት ቀዳሚነታችንን ክደን የእነሱን በዘመናት የተበረዘ እምነት አድናቂና
ተከታይ ስንሆን ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ድህነታችን ከፍተኛ ድርሻ አለው፡፡
ሀይማኖት ለአንድ ሀገር ጥንካሬ ወሳኝነት እንዳለው የማይካድ ነው፡፡ ብዙ ቀኝ ገዥዎች ብዙ አገራትን በቁጥጥራቸው
ሥር ያደረጉት ሀይማኖትን ተገን አድርገው ነው፡፡ በጦርነትና በጉልበት ቢሆን ብዙዎች ባልተሳካላቸውም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ በቅኝ
ግዛት አለመገዛት ሚስጢርም ይሄው ነው፡፡ ክርስትናው ቀድሞ የሕዝቧ ነበርና መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ ማታለል አልሆነላቸውም ይልቁንም ስለእምነትህ
የተባለው ሕዝቧ በኃይል የመጣውን በጽኑ ለመዋጋት ድፍረትና ብቃት ነበረው፡፡ ንጉስ ሶስኒዮስ በጎንደር የካቶሊክ እምነትን የመንግስት
በማድረጉ ሰማዕትነት አያምልጥህ እያለ ሞትን የተጋፈጠው የዚያን ጊዜ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሕዝብ የዚህ አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡
የጣሊያን በኢትዮጵያ ድል መነሳት ምክነያቱም ይሄው ነበር፡፡ ጀግንነት ራሱ እምነት ያስፈልገዋል፡፡ ሀይማኖት የሌለው እንደ እንሰሳ
ነው፡፡ ወደነዱት የሚነዳ፡፡ ክፉ ግን ሊሆን ይችላል፡፡ አላማ ግን አይኖረውም፡፡ ሀይማኖት በታሪክ ብዙዎችን ለመጣል መሳሪያ ሆኗል
ለብዙዎች ደግሞ ጽናት ሆኗል፡፡
ሀይማኖት በአይን ስለማይታዩ ግን በእምነት ይሆናሉ ተብለው ስለሚታሰቡ ጉዳዩች ስለሆነ አብዛኛዎቻችን በእርግጠኝነት
የምንናገረው አይደለም፡፡ አብዛኛው ጉዳይ ደግሞ ስሜት የሚመራው እንጂ ምክነያት እነኳን የሚጠየቅበት አይደለም፡፡ በመሆኑም ሀይማኖትን
አስመልክቶ ጥያቄ ለመጠየቅ ብዙዎቻችን እንፈራለን፡፡ ደፍረን ስንጠይቅም በአብዛኞች የሀይማኖት መሪ ተብዬዎች የሚሰጠን በእርግጥም
ማስጠንቀቂያ አይነት መልስ እንጂ መሠረታዊ ነገሮችን የምናስተውልበትን አቅም አንድናገኝ አደለም፡፡ ብዙ አይጠየቄ ጉዳዮችን ታዲያ
ብዙዎች ለራሳቸው አላማ ሲጠቀሙባቸው ኖረዋል፡፡ የሀይማኖት መሪ ነን ከሚሉት እስከ አገር መሪ በዚህ በማይጠየቁ ውዥምብሮች ውስጥ ተደብቀው በምድር ታላቅ መባልን አግኝተዋል፡፡ በክርስትናውም
(ከጥቂቶች በስተቀር) ይሁን በእስልምናው መንግስተሰማያትና ገሀነም አሉ፡፡ አንደየራሳቸው አስተምሮቶች ደግሞ አንድ ሰው ሀይማኖቱን
ከለወጠ መጨረሻው ገሀነም፤ በእምነቱ ከጸናና መልካም ከሠራ መንግስተሰማያት ነው የሚገባው፡፡ እዚህ ላይ አንድ የመርካቶ የእስልምና
እምነት ተከታይ የሆነ ነጋዴ አለ የተባለውን ቀልድ መሰል ቁም ነገር ላነሳው ወደድሁ፡፡ ሰውዬው ከእስላምና ከክርስቲያን ማን የሚጸድቅ
ይመስልሀል ሲባል ጠያቂውን "ከሁለት አንዳችን አራችንን ሳንበላ አይቀርም" ነበር ያለው፡፡ በእኔ ግምት ይህ ሰው
ነገሩን በውል የተረዳው ይመስላል፡፡ ምክነያቱም እርገጠኛ ነው ገሀነብ አለ፡፡ በአብዛኞቻችን ግን ይህ አይነት ማስተዋል የለንም፡፡
ሀይማኖት እውንም የገሀነብና የመንግስተሰማይ ምርጫ ጉዳይ እንጂ የአባልነት ጉዳይ አደለም፡፡ የብዙ የሐይማኖት መሪ ተብዬዎች ጭንቀት
ስለ አባላቸው መበዛት እንጂ ስለሰዎች የነፍስ ድህነት አይደለም፡፡ አንድ ሰው አሱ ያድናል ከሚለው እምነት ወደ ሌላ ስሄድ ቢቻለው
ሊያጠፋኝ ከዚያ ባነሰ በጠላትነት ሊያየኝ ይችላል እንጂ እኔ ሀይማኖት በመቀየሬ ምክነያት የነፍስ ሞት (ገሀነብ) እንደሚደርስብኝ
አያሳስበውም፡፡ ስለእኔም አዝኖ ወደአምላክ መጸለይ ሳይሆን ይባስ ይረገመኛል፡፡ ለምን እየጠላኝ እንደሆነ መሠረታዊ የሆነ እውነታ
ግን ሊያገኝ የሚችል አይመስለኝም፡፡ የዚህ ሁሉ ምክነያት እራሳችንም እናምነዋለን ስለምንለው አምነት መሠረታዊ ፋይዳውን አልተረዳንውም፡፡
እንደ ክርስትና እምነት ብንወስድ መጽሐፈ ቅዱሱ የሚለው አንዲት ሀይማኖት ነው ግን ዛሬ የሚታየው የሀይማኖት ብዛት
እንዴት በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው እውነታ ሆነ፡፡ እርግጥ ነው
ከመጀመሪያው እንደዛሬ ስም በዝቶለት የነበረ ክርስትና አልነበረም፡፡ ክርስትና ክርስትና ነው፡፡ እየቆየ ሁለት ተከፍሎ ካቶሊክ፣
ኦረቶዶክስ ተባለ፡፡ እያዘገመ የተለያዩ መለስተኛ ልዩነት የሏቸው ሌሎች በተለይም የኦረቶዶክስ ክፍፍሎች ተፈጠሩ፡፡ የካቶሊክ እምነት
ትልቁ መከፈል በ15ኛው መቶ ክፍለዘምን በጀርመናዊው መነኩሴ በነበረው በማርቲን ሉተር በፕሮቲስታንት እምነት መፈጠር ሆነ፡፡ ከፕሮቲስታን
እምነት መፈጠር በኋላ ከፍተኛ የሆነ የክርስትና እምነት መላላት የታየበት ዘመን መጣ፡፡ የፕሮቲስታንት እምነት እልቆ መሳፍርት የክርስትና እምነት አይነቶችን መፈበርክ ጀመረ፡፡ ዛሬ ክርስትና የዕድር ጉባዔ እንጂ የሀይማኖት ጉባዔ አይመስልም፡፡ ማንም
ሰው ዛሬ ተነስቶ እንዲህ ያለ የክርስትና እምነት ልመሰርት ነው ካለ ከልካይ የለውም፡፡ ምክነያቱም ሀይማኖት የሞትና የሕወት ጉዳይ
ሳይሆን የቀበሌ አባልነት ምዝገባ ያህል ቀለላል ሆኖ ታሰበን፡፡ በእምነት አለኝ በሚል እምነት የለሽ እየሆንን እንደሆነ ማስተዋል
አልቻልንም፡፡ የገሀነብና መንግስተሰማያት ነገር ከነ አካቴው ከአእምሯችን ጠፋ፡፡ እኛም ማንነታችንን እየረሳን በሀይማኖት ሰበብ
እንደሌሎች ሁሉ መነዳታችን ግድ ሆነ፡፡
ከላይ እንደተጠቆመው የሀይማኖት ጉዳይ አይጠቄ መሆን በኋላ ለመጣ አይከለከሌ አይነት የሀይማኖት ብዛት ምክነያት እንደሆነ
እናስተውል፡፡ ብዙዎች ለጠየቁት መልስ በማጣታቸው ወይም ይባስ ጃስ በመባላቸው ወይ አዲስ ለእነሱ የሚመች እምነት መመስረት ወይም
እምነት የሚባለውን ነገር እርግፍ አድርጎ መተው አማራጫቸው ነበር፡፡ ሁሉም ክርስትና እንከተለዋለን የሚሉት አንድ መጽሐፍ አነዲት
ሀይማኖት ይላል ግን የቷ? አሁን አለችስ ወይ? ዛሬ ክርስትና ከታሪክ ተያያዥነት የተነጠለ ይመስላል፡፡ ብዙዎቻችን መጸሐፍ ቅድስን
አንብበን ለመረዳት አንችልም ብንችልም አንፈልግም ዝም ብለን ሌላው የሚለንን እየሰማን እምነት ብለን ቁጭ ያልን ስንቶቻችን ነን?
እርግጥ እውቀት እንጂ እምነት በማንበብ ብቻ የሚሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ ማወቃችን ግን ስለምናምነው ነገር እንድናስተውል አቅም ይሰጠናል፡፡ በእርግጥም የእምነት ጉዳይ በመጻሕፍ ሊጠቃለል የሚችል አይደለም፡፡
ብዙዎች ከመጻሕፍ ቅዱስ እየጠቀሱ እንዲህ ይላል እንዲህ አይልም ዋነኛ መለያያቸው ነው፡፡ እውነታው ግን መጽሐፍ ቅዱስ
ራሱ ብዙ ያልያዛቸው እውነታዎች እንዳሉ ነው፡፡ ሲጀምር መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ምን እንደሆነ ለብዙዎቻችን አልተረዳንም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ
ተብሎ ዛሬ በየቤታችን ያለው በተለያየ ዘመንና ሰዎች የተጻፉ መረጃዎች አንድ ላይ ሆነው የተጠረዘ የብዙ መጻህፍቶች ስብስብ እንጂ
አንድ መጸሐፍ እንዳልሆነ ስንቶቻችን እናውቃለን፡፡ በዚህ መጻሕፍ ጥራዝ ሊካተቱ የቻሉት ደግሞ መገኘት የቻሉት ብቻ ናቸው፡፡ ከተገኙትም
በጥራዙ የተካተቱት ክርስቲያን ነን በሚሉ ሁሉ የተሰማሙባቸው ናቸው እንጂ ሳይስማሙባቸው የቀሩት አልተካተቱም፡፡ እንግዲህ ከተጻፉት እንኳን የቀሩ ብዙ አሉ ማለት ነው፡፡ ይህን ዛሬ መጽሐፍ
ቅዱስ ተብሎ ያለውን ስናነብ ራሱ ብዙ የቀሩ መረጃዎች እንዳሉ እንረዳልን፡፡ በብሉይ መጻሕፍት የቀረው የእከሌ ታሪክ በእንዲህ ያለ
መጽሐፍ ይገኛል በእንዲሕ ያለ የትንቢት መጻሕፍ ይቀኛል ይላል፡፡ የትንብት የተባሉት መጸሕፍት እንኳን ያልተካተቱ አሉ ማለት ነው፡፡
ወደ ወንጌል ስንመጣ ከፍተኛ የሆነ የታሪክ ክፍተት ይታይበታል፡፡ አራቱም ወንጌላውያን ስለክርስቶስ ምድራዊ ታሪክ ሙሉ መረጃውን
አይሰጡም፡፡ ትንሽ መነሻ ታሪክ ሊጽፍ የሞከረው ሉቃስ ጌታን ሲወለደ፣
12 ዓመት ሲሆነው ከዚያ ሁሉም የጠቀሱትን ከጥምቀቱ በኋላ ያለውን ታሪክ ነው ሌሎቹ ግን ተወለደ ተጠመቀ ነው ብለው የጻፉት፡፡
እርግጥ እነዚህ ጸሀፊዎች ጌታን እውንም የተከተሉት ከጥምቀቱ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም በኋላ ቢሆን በየቀኑ ስለነበረው ነገር የጻፉት
አይደለም ዛሬ ወንጌል ሆኖ የምናነበው፡፡ ይልቁንም ጌታ ከአረገ አመታት በኋላ (20ና ከዚያ በላይ አመት) ወደኋላ እያስታወሱ የጻፉት
ነው፡፡ የሚያወራው፡፡ ስለወለደችው እናቱ እንኳን ማንነትና የዘር ሀረግ መጻሕፍ ቅዱስ አይናገርም፡፡ በተሸለ በእስልምናው የቁራን
መጽሐፍ የጌታ እናት ታሪክ ተዘግቧል፡፡ ይህ እንግዲህ ብዙ ያልተጻፉ ጉዳዮች እንዳሉ የምንረዳበት ነው፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ ይህንኑ
አስመልክቶ ጌታ ያደረጋቸውን ሁሉ ለመጻፍ ወረቀት እንደማይበቃ ጠቁሟል፡፡
ሌላው ጸሐፊዎቹ በወቅቱ የነበረው ባህልን ተክትለው ስለጻፉ አሁን ላለንወ ገር የሚሉን ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የጌታ
የትውልድ የዘር ሀረግ በዚያን ጊዜ በነበረ ባሕል ሊሆን ተጽኖ ሊሆን ይችላል በወለደችው እናቱ የዘር ሀረግ ሳይሆን በሰውኛው በደም
በማይዛመደው ዮሴፍ በኩል ነበር የተቆጠረው፡፡ እርግጥ ክርስቶስ በእናቱ በኩል ዛሬም ያለንውን ጨምሮ በደም የተዛመደ ነው፡፡ ጸሀፊዎቹ
ግን ይህንን አስበው ሳይሆን በወቅቱ የነበረው ባሕል ተፅኖ ነው ሥጋዊት እናት እንጂ ሥጋዊ አባት እንደሌለው እያወቁ የዮሴፍን ዘር
ሀረግ የተከተሉት፡፡ ሌላው ደግሞ ጸሀፊዎቹ ትኩረት ያደረጉበት ጉዳይ
ለጻፏቸው መረጃዎች ምክነያት ነበሩ፡፡ አራቱን ወንጌላት ስናይ ማቴዎስ የጌታን ትምህርት፣ ማርቆስ ተዓምራቱን ሉቃስ ታሪኩን፣ ዩሐንስ
የጌታን ማንነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ይመስላል፡፡ የጌታ እግዚአብሔርነት በግልጽ የሚነበበው በዮሐንስ ወንጌል ነው፡፡ ይህም ለጌታ
ከሁሉም ሐዋርያት ይልቅ ቅርብ ስለነበር ጌታ ራሱ ለኋላ ምስክርነት እንዳዘጋጀው እንረዳለን፡፡ ሌላው ወንጌል አራት ብቻ ነው ወይ
የሚል ጥያቄም ሊያስነሳ የሚችል በወቅቱ የነበረ ነባራዊ ሁኔታ የጴጥሮስ የሆነ ጽሑፍ ስለጌታ የምድር ውሎ ምንም አለመነበቡ ነው፡፡
ሌሎች ቀሪዎቹም ቢሆኑ የተወሰነ መረጀ ጽፈው እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ ከሐዋሪያት ዘመን በኋላ ያለው የክርስትና ሂደት ታሪክ
ደግሞ ሌላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለተካተተ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙዎቻችን እንደሚመስለን አንድ መጻህፍ ከለመሆኑ ባሻገር አሁን
በምናየው ጥራዝ መልክ የተዘጋቸው በሐዋርያት ዘመን ሳይሆን ከሐዋርያት በኋላ 300 ዓመት አልፎ ነው፡፡ የመጻሕፍ ቅዱስ ታሪኮች
ሁሉ ከ2000ና ከዚያ በላይ ያሉ ታሪኮች ናቸው፡፡ የክርስትናው ዋና ታሪክ ደግሞ ከዚያ ወዲህ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ግን ለብሉዩም ለሐዲሱም ዘመን ካላት የታሪክ ቅርበት አንጻር በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተካተቱትንም የክርስትናውንም አጀማመር እንዴት እንደነበር ለማመሳከር የሚያስችሉ በርካታ
መጻህፍት እንደያዘች የዘመኑ የታሪክና የቅርስ ጥናት ጠበብቶች ሳይቀር የሚመሰክሩት እውነታ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ግን በብዙ በተለይም
ሐይማኖትን መሳርያ አድርገው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ትልቅ መነቆ እንደሆነባቸው ስለገመቱ ይህ ሀይማኖታው ታሪክ በዚች አገር እንዲቀጥል
አይፈልጉም፡፡ የአሁን ጊዜ ዋነኛ ዘመቻቸውም የእነዚህ ቁልፍ የሀይማኖት ሚስጢራት ማሕደር የሆነቸውን የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያንን
መበረዝ፣ ማዳከም፣ በመጨረሻም የእነሱን ፍልስፍና እንደፈለጉ ሊሰብኩት የሚችል ትውልድን በዚች አገር መቅረጽ ነው፡፡ የእምነት ዘመቻውን ድራማ ስናይ የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ለማዳከም አንድ
በሆኑት የፕሮቴስታንት እምነት ተቋማት መካከል ያለው ልዩነት ከስላሴ (የሶስትነት-አንድነት) እምነት፣ እስከ ኢየሱስ ብቻ፣ አስከ ክርስቲያን ነን የሚሉ ግን የጌታን አምላክነት የማይቀበሉ
የእምነት ልዩነት ያላቸው ናቸው፡፡ የኦረቶዶክስ ተከታይ ነኝ ባዩም ከመሠረታዊ እምነቱ ይልቅ ባህልና የክፉ መናፍስትን መከተል ሳይቀር
የቀላቀለ ስለሆነ ለሌሎች ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል፡፡ እምነትን ከነፍስ
ድህነት ጋር ሳይሆን ለስጋችን ተድላ ብቻ በማሰብ ጠፍተናል፡፡
ይቀጥላል!
አንባብያን የታላ ቋ ቀን ልጅ አንድ ጊዜ ይጽፋል
እንጂ ደግሞ አያርመም! በአማርኛ ሶፍትዌር የፊደላት ግድፈትም ይቸገራል፡፡ በመሆኑም ለሚፈጠሩ የፊደላትና ቃላት ግድፈት ይቅርታ
ይጠይቃል፡፡
አቤቱ አባት ሆይ መሠረታችንን እናውቅ ዘንድ ማስተዋልን ስጠን! አእምሮአችንን ክፈት! አሜን!
የታላቋ ቀን ልጅ ጥቅምት 22ኛውቀን 2006 (Son of the great day the 1st
of November 2013)
No comments:
Post a Comment