የጋራ ማሕበር ለመመስረት የተስማማሙት ፖለከኞች እንደሚሉት የመጨረሻ አላማቸዉ ቢቻል ሁሉንም በሰላማዊ መንገድ
የሚታገሉ ተቃዋሚዎችን ይሕ ቢቀር ሰላሳ ሰወስት ፓርቲዎችን አስተባብሮ አንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ጎራ ለመፍጠር ነዉ።ይሕ
ምናልባት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተቃዋሚዉ ጎራ የሚታየዉን መከፋፋል፥ መሰነጣጠቅና መጠላለፍ ለማስቀረት ይረዳ
ይሆን?
አስር የሚሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ ማሕበር ወይም ቅንጅት ለመመሥረት
ተስማምተዋል።አደራጆቹ እንደሚሉት አሁን የጋራ ሕብረት የሚመሠርቱት ፓርቲዎች በሒደት በርካታ ፓርቲዎችን
ከሚያስተናብረዉ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ መድረክ ጋር የጋራ ትብብር ወይም ሕብረት የመመስረት እቅድ
አላቸዉ።የጋራ ሕብረት ከሚመሠርቱት መካከል ደግሞ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና አንድነት
ለዲሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ለመዋሐድ እየተወያዩ ነዉ።የጋራ ማሕበር ለመመሥረትም ሆነ ለመዋሐድ በሚደረጉት
ዝግጅቶችና ዉይይቶች የማይሳትፉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ ሒደቱን ከሩቅ ማየቱን መርጠዋል።የዉይይት ዝግጅታችን
የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የትብብር እንቅስቃሴና የኢትዮጵያ ፖለቲካን ባጭሩ ይቃኛል።
በመሠረቱ የፖለቲካ መርሕ፥ ዓለማን ከግብ
የማድረሻ ሥልትና ስትራቴጂን ዘመን፥ ሕዝብ እና የየዘመኑ ትዉልድ ከሚጠይቅ ወይም ከሚፈልገዉ ጋር ለማጣጣም ማሻሻል፥
ማረቅ፥ ማስተካከል የድፍን ዓለም ፖለቲካዊ ወግ ነዉ።የፖለቲካ አቋማና አሠላልፍን መለወጥም ከፖለቲከኛዉ ፖለቲካዊ
ሥብዕና አንዱ መሆኑን ብዙዎች ይስማማበታል።የኢትዮጵያ ግን ብዙዎችን ከሚያስማማዉ ፈንገጥ ያለ ይመስላል።ከ1960ዎቹ ወዲሕ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ብቅ ያሉ ፖለቲከኞች ካንጀት-ይሁን ካንገት ለፖለቲካ ፍጆታ ይሁን ከምራቸዉ በዉል ለማወቅ ቢከብድም በየፊናቸዉ ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔር ተወላጆች፥ የተለያየ ሐይማኖት ተከታዮች ተቻችለዉ የሚኖሩባት ሐገር መሆኗን እየነገሩን፥ በገቢር ግን እራሳቸዉ አለመቻቻላቸዉን እያሳዩን ነዉ።
ብዙ ፖለቲከኞች ሊቀየሙ ወይም ቅር ሊላቸዉ ይችላል።እዉነታዉ ግን ይሕ ነዉ። አንድ ወይም ተመሳሳይ ርዕዮተ-ዓለም፥ መርሕ አላማ መያዛቸዉን የሚያዉጁ ኢትዮጵያዉያን ፖለቲከኞች የመንግሥት ሥልጣን የያዙ ይሁኑ፥ የነፍጥ ተዋጊዎች፥ ሠላማዊ ታጋዮች፥ ስደተኞች አብረዉ ለመስራት መቁረጥ መስማማታቸዉን በሰማን ማግስት መለያየት፥ መጣላት፥ሲከፋም መገዳደላቸዉን ያልሰማንበት ጊዜ የለም።ካለም አጭር ነዉ።
በአንፃራዊ መመዘኛ ኢትዮጵያ የተሻለ የሚባል ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ካስተነጋደችበት ከ1997ወዲሕ ክፍፍል፥ ጠብ መወነጃጀሉ በሁሉም ደረጃ ባሉ ፖለቲከኞች ዘንድ ቢታይም በተቃዋሚ ጎራ በተሰለፉት ላይ ጎልቶና ተደጋግሞ ይታያል።ምክንያቱ በርግጥ ጥልቅ ጥናንት ሰፊ ክርክር ዉይይት የሚሻዉ ጉዳይ ነዉ።ሰሞኑን ከአዲስ አበባ የሰማነዉ ደግሞ ለየት ያለ ነዉ።ወደ አስር የሚሆኑ (ቁጥሩ ትንሽ ግልፅ አይደለም) ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ግንባር፥ ሕብረት፥ ወይም ቅንጅት ለመመሥረት ተስማምተዋል።ወይም ዉይይት ጀምረዋል።
የጋራ ማሕበር ለመመስረት የተስማማሙት ፖለከኞች እንደሚሉት የመጨረሻ አላማቸዉ ቢቻል ሁሉንም በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ተቃዋሚዎችን ይሕ ቢቀር ደግሞ እስካሁን ድረስ ጊዚያዊ የትብብር የመሠረቱትን ሰላሳ ሰወስት ፓርቲዎችን አስተባብሮ አንድ ጠንካራ ተቃዋሚ ጎራ ለመፍጠር ነዉ።ይሕ ምናልባት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተቃዋሚዉ ጎራ የሚታየዉን መከፋፋል፥ መሰነጣጠቅና መጠላለፍ ለማስቀረት ይረዳ ይሆን? መልስ የሚሰጡን እንግዶች ጋብዘናል።
ነጋሽ መሐመድ
ልደት አበበ
dw.de
No comments:
Post a Comment