Thursday, November 7, 2013

የመፀሃፍ ግምገማ: “ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” – ደራሲ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ


- ግምገማ በጥላሁን አፈሣ

(PDF) ብርሃኑን ከ ፳፭ አመታት ላላነሰ ግዜ በቅርብ የማውቀው ጓደኛየ ነው። ለሥራ ትጋቱ፣ ለቆመለት አላማ ፅናቱ፣ የማይረግበው የይቻላል መንፈሱ፣ ካወቅኩት ግዜ ጀምሮ ያልተለዩት መላያ ባህርዮቹ ናቸው። በእነዚህ አምታት ውስጥ፣ የአገሩን ጉዳይ በሚመለከት የተሳተፈባቸውንና ያከናወናቸውን መጠነ ሰፊ ተግባሮች መዘርዘር ይህ ቦታው ባይሆንም፣ በዚህ አጋጣሚ፤ እንደው በጥቅሉ ብርታቱን የሰጠው ግለሰብ መሆኑን በጨረፍታ ገልጬ ማለፍ እወዳለሁ። ሌላው ቢቀር ፣ የራሱን የግል ነፃነት ተነፍጎ፣ የነፃነት ጭላንጭል በማይታይበት በቃሊቲ ወህኑ ቤት ነዋሪ በነበረባቸው በነዛ ሁለት ፈታኝ ዓመታት ውስጥ፣ “የነፃነት ጎህ ሲቀድ” በሚል ርዕስ በቁርጥራጭ ወረቀቶች ላይ ከትቦ ገና ከቃሊቲ ሳይሰናበት ለህትመት አብቅቶ ያቋደሰንን ከ ፮፻ ገፆች በላይ ያካተተውን መጸሃፉን በማንበብ ብቻ፣ በእርግጥም ብርታቱን የሰጠው ሰው መሆኑን መገንዘብ አያዳግትም። በተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ላይ ሆኖ በፃፋት በዛች ድንቅና ተስፋ ጫሪ መጽሃፉ መግቢያ ላይ፣ “ከአሜሪካ ኑሮዬ የተገነዘብኩት የነፃነት እና የኢኮኖሚ ብልፅግናን ጠንካራ ግንኙነት ነበር”፤ አገር ቤት ከተመለሰኩ በሗላ በጻፍኳቸው የተለያዩ ጽሑፎቼም “የዴሞክራሲ እና የኢኮኖሚ እድገት ትስስርን በሚመለከት በአጠቃላይና በተለይ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ብልፅግና የዜጎች ነፃነትና ዴሚክራሲያዊ ስርዐት አስፈላጊነትን መክሪአለሁ” በማልት በጽኑ የሚያምንበትን መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ አስምሮበት አልፎ ነበር።
Democracy-and-Development-in-Ethiopia-Standing-Book1 brehanu nega“ዴሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” ብሎ በሰየማት በዚች ሁለተኛው መጸሃፉ ውስጥም እንዲሁ፣ “የአሜሪካን የፖለቲካ ስርዓት በገቢር በማየት የስርዓቱ የማዕዘን ድንጋዮች የህዝቡ የተለየ ጥሩነት፣ የፖለቲከኞቻቸው ልዩ ችሎታና ብስለት ሳይሆን ስርዓቱን ተሸክመው በያዙት ተቋማት ላይ መሆኑን አምኛለሁ። የተቋማት ጥንካሬ፣ የተቋማት ነፃነት፣ ከግለሰቦች ይልቅ ለተቋማት የሚሰጠው ክብርና ታማኝነት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እውን ለማድረግ እጅግ አስፈላጊው መሳሪያ መሆኑን በፊት ከማምነውም የበለጠ ያለምንም ጥርጣሪ እንድረዳው አድርጎኛል” በማለት ገልጾልናል። ይህን መሰረታዊ እምነቱንም ነው በዚች መጸሃፉ ውስጥ በሰፊው በምክንያታዊ ትንተና የተደገፈ ሃተታ የሰጠበት።
ብርሃኑ ይህችን መጸሃፍ ለህትመት ከመብቃቷ በፊት፣ የመጀመሪያውን ንድፍ ልኮልኝ አስተያየቴን እንድሰጠው ጋበዞኝ ስለነበር፣ በኔ አስተያተት፣ መጸሃፏ ወቅታዊና መሰረታዊ በሆኑ የአገራችን ችግሮች ላይ ያነጣጣረችና የተለመችውን ኢላማ በብቃት የመታች መሆኑን ጠቁሜው በአስቸኳይ ለህትመት እንዲያበቃት ጎትጉቸው ነብር። ለህትመት ስትበቃም፣ በሽፋኗ ጀርባ ላይ ባጭሩ ከሰፈረው ስለመጸሃፏ ያለኝ አጠቃላይ አስተያየት ውስጥ፣ “የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል ማንም ሰው ይህን መጽሃፍ በክፍት አዕምሮ ማንበብ ብቻ ሳይሆን አንብቦም ከሌሎች ዜጎች ጋር የምር ውይይት ማድረግ ይጠበቅበታል” የሚል ይገኝበታል። በዚች መጻጽፍም ፣ መጽሃፏ ካዘለቻቸው በዛ ያሉ ቁምነገሮች ውስጥ መሰረታዊ ናቸው ብየ ባመንኩባቸው ሁለት ነጥቦች ላይ አተኩሬ አስተያየቴን በማቅረብ አንባቢን ለውይይት እጋብዛለሁ። ወደ እነዚህ ሁለት ነጥቦች ይዤያችሁ ከመጓዜ በፊት ግን፣ የመጸሃፏን አጠቃላይ ይዘት አንባቢው እንዲረዳ፣ በአምስቱም የመጸሃፏ ምዕራፎች ሥር ደጋግመው ተንጸባርዋል የምላቸውን መሰረታዊ ሃሳቦች ባጭሩ እቃኛለሁ።
ብርሃኑ፣ የዚች መጽሃፍ አላማ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ዴሚክራሲያዊ ካልሆኑ ስርዓቶች በሁሉም መስፈርት የተሻለ እንደሆነ ማስረዳት መሆኑን በዚች መጸሃፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ገልጾልናል። ይህንንም አወንታ፤ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታዎች ለናሙና እያቀረበና ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚና ከአካባቢ ጥበቃ ችግሮች ጋር እያዛመደ፣ ለአንባቢ በማይሰለች ብዕር፣ በሰፊው፣ በብቃትና በጥራት በመተንተን እንድንረዳ አድርጎናል። በዚህም ጉዞው፣ በመጀመሪያ የአምባገነን ሥርዓቶች መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው፣ ለአገር ልማትና ግንባታ የዴሞክራሲ መኖር ወሳኝ አለመሆኑን ለማሳየት የሚጠቀሙበትን መከራከሪያ ሃሳቦች በማቅረብ፣ የነዚህን ሃሳቦች ብኩንነት በወጉ እያገላበጠና እያደቀቀ በአምስቱም የመጸሃፉ ምዕራፎች ሥር በረድፍ በረድፉ አካቶ አመርቂ ትንታኔ አቅርቦበታል።
ብርሃኑ በዚች መጽሃፍ ላይ ያተኮረው፣ ለኢትዮጵያችን የሚያስፈልገው የትኛው አይነት የኢኮኖሚ ስርዓት ነው የሚለው ላይ ሳይሆን፣ የሚሻለውን ለመምረጥ የሚኬድበት ሂደት ላይ ነው። እንደብርሃኑ እምነት፣ ይህ “ደግሞ ባብዛኛው የሚመለከተው የፖለቲካ ሥርዓቱን” ስለሆነ፣ “በኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ላይ የሚደረግ ትርጉም ያለው ውይይት በመጀመሪያ መመለስ ያለበት ይህንን ጥያቄ ነው።” ስለዚህም ይመስለኛል፣ የመጀመሪዎቹን ከመቶ ገጾች በላይ ያካተቱ ሁለት ምዕራፎች በፖለቲካው ጥያቁዎችና ችግሮች ላይ እንዲያጠነጥኑ ያደረገው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሥር፣ አንድን የፖለቲካ ስርዓት ጥሩ የሚያሰኙትን ንጥረ ነገሮችና ከነዚህ ውስጥ የአገራችን የፖለቲካ ስርዓት አላሟላቸውም የሚላቸውን መስፈርቶች በሰፊው አትቶባቸዋል። እነዚህን የጥሩ ፓለቲካ ስርዓት አመልካች የሚላቸውን አምስት መሰረታዊ መስፈርቶች ለእያንዳንዳቸው ንዑስ ክፍል በመስጠት ሰፋ ያለ ትንታኔ አቅርቦማቸዋል። ይህን ምዕራፍ ሲያጠቃልልም፣ “ማህበረሰቡ ከጥቂት ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች ባሻገር ለሃገሩና ለፖለቲካ ስርዓቱ ታማኝ የሆኑና የባለቤትነት ስሜት የሚሰማቸው ዜጎችን በቀጣይነት ማፍራት የሚችለው” ሥርዓቱ እነዚህን ጥሩ የሚያሰኙትን መሰረታዊ መሥፈርቶች ሲያሟላ ብቻ መሆኑን አስምሮበት ነው። እነዚህን ዋቢ መስፈርቶች መጸሃፉን በማንበብ በሰፊው ልትተዋወቋቸው ስለምትችሉ፣ እዚህ መዘርዘር አስፈላጊ አይመሰለኝም።
Dr. Birhanu Negaየሁለተኛው ምዕራፍ ትኩረት፣ እነዚህን መሰረታዊ መሥፈርቶች ለማሟላት ሲፈለግ የሚያጋጥሙ መሰናክሎችን መቃኘት ነው። በዚህ ምዕራፍ ሥር ፣ “የማንነት ፖለቲካ”በአገራችን ዲሞክራሲያዊ ሥርዐት ምሥረታ ላይ ያሳደረው ተጽእኖ የችግሮቹ ሁሉ ቁንጮ ለመሆኑ ያለውን ግንዛቤ በሰፊው አትቶበታል። ይህን ትንተናውን ያካተተው ደግሞ “የታሪክ ጠባሳ” በሚሉ ሁለት ቀልብ ሳቢ ቃላት በሚጀምር ንዑስ ርዕስ ስር ነው። ታሪክ ትቶልን ያለፈውን “ጠባሳ” ከመግለጹ በፊት ግን፣ የመጀመሪያዎቹን አምስት ገጾች በመንደርደሪያነት በመጠቀም ታሪክ ምንድን ነው? የሚለውን መስቀለኛ ጥያቄ ይቃኝል። ይህን ቅኝት ተመርኩዞም፣ በታሪክ ላይ ተመስርቶ የዛሬውን የጋራ ህይወት ለመቅረጽ የሚደረግ ሙከራ ሁሌም ችግር ውስጥ የሚገባ ስለሆነ፣ የታሪክ ዘገባውን ለታሪክ ሰዎች ትተን፣ ለችግሩ የፖለቲካ መፍትሄ እንድንፈልግለት ይማፀነናል። ብዙም ሳይቆይ ግን፣ ይህንኑ የማንነት ፖለቲካ አሰመልክቶ በሁለት አቢይ ተዋንያን የህብረተብ ወገኖች የሚተረኩ ታሪኮች የሚላቸውን ይዞልን ይቀርባል። በዚህ ጊዜ ግን፣ እኛ እንድንሸሸው የተማጠነንን በታሪክ ላይ የተመሰረተ ዘገባ፤ እራሱ ማምለጥ የቻለ አልመሰለኝም። አስተያየቴን አቀርብባቸዋለሁ ካልኩት ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች ውስጥ የመጀመሪያው በዚሁ የብርሃኑ የታሪክ ዘገባ ላይ ያጠነጠረ ስለሆነ፣ እመለስበታለሁና እዛው እስክደርስ አብራችሁኝ እንድትጓዙ በትህትና እጠይቃለሁ።
ብርሃኑ፣ በመጽሃፉ ሶስተኛ ምዕራፍ ሥር ፣ ጥሩ የሚባል የኢኮኖሚ ስርዓት ማካተት አለበት የሚላቸውን ንጥረ ነገሮችን በብቃትና በሰፊው ትንተና ያቀርብበታል። ይህን ሲያደርግም፣ ጥሩና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ስርዓት የትኛው ነው የሚለውን አከራካሪና ፍልስፍናዊ መልስ የሚሻ ጥያቄ ወደጎን ትቶ፣ በኢኮኖሚ ፍልስፍና ላይ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ሁሉ በጋራ ይሰማሙባቸዋል ብሎ የሚያምንባቸውን ንጥረ ነገሮች ብቻ በመቃኘት ነው። ብርሃኑ ይህን ስሌት የመረጠበትን ምክንያት ሲያስረዳ፣ መጽሃፏ በዋናነት እንድታነጣጥር የተለመበትን አቅጣጫ እንዳትስት ለማረግ መሆኑን ይገልጻል። በራሱ አባባል፣ “የተለያየ የግል ጥቅም ያላቸው ሰዎች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ” እና “በተለያየ መስፈርት ሲለኩ ብዙ አማራጭ መፍትሄዎች በሚኖሩበት ሁኔታ ጥሩውን እንዴት ነው የምንመርጠው? በሚለው የሂደት ጥያቄ ላይ እንድናተኩር ነው።” ይህን ምዕራፍ ሲቆጭም፣ የኢኮኖሚው ስርዓት እነዚህን መሰረታዊ ንጥረ ነገሮች ማካተቱ የሚለካው፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲው አወጣጥም ላይ ሆነ አተገባበር ላይ፣ የማህበረሰቡን አጠቃላይ ጥቅም የሚያስቀድም፤ ለማንም የተለየ ቡድን አድልዎ የማያደርግ መንግሥት መኖር ሲችል ብቻ ነው በማለት አሁንም የሂደት ጥያቄ በመጀመሪያ መመለስ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ መሆኑን በጎላ ድምጽ በማሰማት ነው።
ምእራፍ ፬ ጥሩ የኢኮኖሚ ስርዓት በአገራችን ለመገንባት ያሉብንን መሰረታዊ መዋቅራዊ ችግሮች በአራቱም የጥሩ ኢኮኖሚ መለኪያ መስፈርቶች አኳያ በመመዘን ይፈትሽና በነዚህ መሥፈርቶች ስትለካ ሀገራችን ፍጹም ሗላ የቀረች መሆኗ ብዙ የሚያከራክር ጉዳይ አለመሆኑን ያስረዳል። እነዚህ ዘርፈ ሰፊ የአገራችን ችግሮች፣ መንግሥት ስለተቀየረና ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ስለተመሰረተ በቶሎ የሚጠፉ ስላልሁኑ፣ ለማንኛውም አይነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥርዓት ፈታኝ እንደሚሆኑና አመርቂ መልስ የሚሹ መሆናቸውን ልብ ልንል ይገባል ሲል ያሳስበናል። አሁንም ለብርሃኑ ዋነኛው ቁምነገር፣ ከብዙ የፖሊሲ አማራጮች ውስጥ፣ የፖለቲካ ስርዓቱ የትኛውን መፍትሄ እንዴት ይመርጣል የሚለው የዚያን የፖለቲካ
ኢኮኖሚ ምንነት የሚያሳይ አይነተኛ ገላጭ መሆኑን መገንዘብ መቻላችን ነው። በአመራረጥ ሂደቱ ላይ ያልተስተካከለ የመወዳደሪያ ሜዳ፣ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረውን አሉታዊ ውጤት ሲተነትንም ውጤቱ በሙስና ግዙፍ ጫና የተቀፈደደ ጭንጋፍ ኢኮኖሚ እንደሚሆን ለአንባቢ መረዳት ዳገት ባልሆነ ትንተና አስረድቶናል። በዚሁ ምዕርፍ ሥርም፣ ስለ እድገት/ልማትና የልማታዊ መንግሥት ከአርሶ አደሩና ከአርቢው መደብ መሬት መፈናቀል በሰፊው ዘክሮበታል። ይህን ምዕራፍ ሲያጠቃልልም፣ የኢኮኖሚ ችግሮቻችን ብዙ ቢሆኑምና እነዚህን መጠነ ሰፊ ችግሮቻችንን መፍታት ቀላል ባይሆንም ቅሉ፣ ሂደቱን በጥንቃቄ ካዘጋጀነው መፍትሄው ከችሎታችን ውጪ አንዳይደልና ተስፋችንን ጨለምተኛ እንዳናደርገው ምሁራዊ ምክሩን በመለገስ ነው።
ብርሃኑ በምዕራፍ ፭ ስር የአካባቢ ጥበቃ ችግሮቻችንን አስመልክቶ፣ የህዝብ ብዛት፣ የአየር ፀባይ መቀየር፣ የደን መመናመን፣ የመሬት መሸርሸር/መከላት የሚያመጡትን ችግሮች አገሪቷ ካለችበት ሁኔታ ጋር አዛምዶ አሁንም ሰፋ ያለ ትንተና አቅርቦበታል። በብርሃኑ እምነት፣ እነዚህ መጠነ ሰፊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል ተቀባይነት ያለው እቅድ መንደፍ የሚቻለው፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እራሳቸው በመረጧቸው ወኪሎቻቸው አመካኝነት በሰጥቶ መቀበል ሂደት ተወያይተውበትና ተከራክረውበት ለብዙሃኑ የሚበጀውን ውሳኔ መስጠት ሲችሉ ብቻ ነው። ይህንን ምዕራፍ የሚደመድመውም፣ መፍትሄው ላይ ከመድረሳችን በፊት፣ ዋናው ጥያቄ ወደመፍትሄው የምንጓዝበት ሄደት መሆኑን ለአንድ አፍታም መዘንጋት እንደሌለብን በመጠቆም ነው።
ይህችን አጭር ግምገማ በወጉ ያነበበ ሁሉ ሊረዳው እንደሚችለው፣ ብርሃኑ፣ ሳይሰለች በአምስቱም ብዕራፎች ሥር ደጋግሞ የነገረን መሰረታዊ እምነቱ፣ ለጥያቄዎቻችን በዛ ያሉ ተወዳዳሪ መልሶች፣ ለችጎሮቻችን ብዙ አማራጭ መፍትሄዎች በሚኖሩበት ሁኔታ፣ መፍትሄውን ለመፈለግ የምንጓዝበት ሄደት ዴሞክራሲያዊ መሆን ወሳኝነት እንዳለው ነው። መፀሃፉን አጠቃሎ በማሳረግ የተሰናበተንም፤ “ከእወነተኛ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውጪ ማህበራዊ ልከኛ የሆነ መፍትሄ ሊሰጠን የሚችል ሌላ የፖለቲካ ስርዓት የለም። ይህን ስርዓት በኢትዮጵያ መመስረት ለሁሉም አይነት ማህበረሰባችን ችግሮች የመፍትሄው መጀመሪያ ብቻ ሳይሆን፤ የመፍትሄው ዋና ቁልፍ ነው” በማለት ነው። የሁለተኛው ትዝብታዊና ጥያቄ አዘል አስተያየቴም፤ ብርሃኑ መሰረታዊ እምነቱ መሆኑን ሳያሰልስ ባስታወቀንና እኔም እሰየው ብየ በምቀበለው የዴሞክራሲያዊ ሂደትን ወሳኝነት ከሚያረጋግጠው ንጥረ ሃሳብ ጋር የተያያዘ ይሆናል። አሁን በቀጥታ ወደ አስተያየቶቼ ይዣችሁ ላዝግም።
“በማንነት” ጥያቄ ላይ
ብርሃኑ፣ የ “ማንነት”ን ጥያቄ አሰመልክቶ ያቀረበውን ትንተና ያካተተው “የታሪክ ጠባሳ” በሚሉ ሁለት ቀልብ ሳቢ ቃላት በሚጀምር ንዑስ ርዕስ ስር መሆኑን ቀደም ብየ ጠቁሜያለሁ። በኔ አስተያየት፣ የብርሃኑ የታሪክ አተረጓጎም ችግር የሚጀምረው ከዚህ ነው።
ጠባሳ የደረቀን ቁስልን አመልካች ነው። ይህ አባባል፣ ብርሃኑ በዚህ ምዕራፍ ሥር ያተኮረበት የወቅቱን የኦሮሞ ብሄረሰብ ጥያቄ በተመለከተ ፣ የሚሰጠው ፍቺ የታሪክ ቁስላችሁ ደርቋል የሚለውን ነው። የኦሮሞ ብሄረተኞች ፣ ቁስላችን አልደረቀም ብቻ ሳይሆን፣ እያመረቀዘ ያለ ሰለሆነ፣ በወቅቱ መድሃኒት ካልተተኘለት ከጊዜ በሗላ መላ ፖለቲካዊ ሰውነታችንን ወሮና አጠቃላይ አገራዊ ህልውናችንን ሸርሽሮ ሊገነጣጥለን የሚችል ሞገደኛ በሽታ ነው የሚሉት። ኦሮሞ ያልሆንነውንና “ዴሞክራሲያዊ“ ሃገራዊ ብሄረተኞች ነን የምንለውን የሚጠይቁት፣ ቁስላችው እንዲሰማን አይመስለኝም። እኔ እስከተረዳሁት ድረስ፣ እየነገሩን ያለው፣ ቁስላችን አሁንም ድረስ ይሰማናል ስንላችሁ ስሙን እንጂ። መሠማማት የሚቻለውና መሥማማት ላይ የሚደረሰው፣ በመጀመሪያ መሥማት ሲቻል ነውና አስቀድማችሁ ጆሯችሁን ለግሱን ነው የሚሉን የሚመስለኝ ። በኔ ግምት፣ ብርሃኑ ቃሉን በገላጭነት የተጠቀመበት ትርጉምን ሳያውቅ ቀርቶ ሳይሆን፣ በዚህ ጥያቄ ላይ እራሱ ለሚተርከው ታሪክ ጠባሳ ከቁስል የተሻለ ቅርበት ያለው መግለጫ ሆኖ ስላገኘው ይመስለኛል። ይህን ያልኩበትን ምክንያት ላስረዳ። ለዚህ እንዲረዳኝ፣ በመጀመሪያ ብርሃኑ የተዋንያኖቹን ማንነት የገለጸበትን ስሌት ልመዝግብ።
zehabesha

No comments:

Post a Comment