Wednesday, November 6, 2013

ጅጅጋ የበዓል ዝግጅትና ወከባ


ጸጥታ አጠባበቁ በተለይ በእጅጉ መጠናከሩም ተሰምቷል። ከዚሁ የተነሳ ኣንዳንድ የከተማይቱ ኗሪዎች ፍተሻው እና ወከባው በዝቶብናል ሲሉም ያማርራሉ። አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የጅጅጋ ከተማ ኗሪ ደግሞ የተመቱ እና የተዘረፉም አሉ ይላሉ።የክልሉ የማስታወቂያ እና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሐመድ ጎሬ ግን ይህ መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ አስተባብሏል።
በየዓመቱ በዚህ ወር መጨረሻ የሚከበረረው የኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች ቀን የዘንድሮው በሶማሌ ክልል ሊከበበር ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ መሆኑ ተነገረ።በተለይም የጸጥታው ቁጥጥር እጅግ የተጠናከረ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንድ የጅጅጋ ከተማ ኗሪዎች ወከባ በዝቶብናል ሲሉ ያማርራሉ።በክልሉ የተረጋጋ ሰላም መኖሩን የገለጸው የክልሉ መንግስት ግን የተባለውን ቅሬታ መሰረተ ቢስ ነው ሲል አስተባብሏል።ከኢትዮጵያ መንግስት አንጻር ነፍጥ የመዘዘው የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ONLF በክልሉ በመንግስት ወታደሮች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየሰነዘርኩ ነው ሲል በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል።

የብሄር ብሄረ ሰቦች ቀን በኢትዮጵያ መከበር የጀመረው እየተሰራበት ያለው የኢትዮጵያ ህገመንግስት የጸደቀበትን ወርና ዕለት መሰረት አድርጎ ሲሆን ዓላማውም የመንግስት ባስልጣናት እንደሚያስተዋውቁት ከ80 በላይ ብሄረሰቦች በሚገኙባት ኢትዮጵያ ህዝቦች እርስ በእርሳቸው ይበልጥ እንዲተዋወቁ ልምድ እንዲለዋወጡ በእኩልነት ላይ ለተመሰረተ አንድነትና የጋራ ልማት ቃላቸውን የሚያድሱበት አጋጣሚ ነው።

አከባበሩም በየዓመቱ በተለያዩ ክልሎች እየተዘዋወረ ሲሆን የዘንድሮው ደግሞ የሚከበረው የሶማሌ ክልላዊ መንግስት መቀመጫ በሆነችው ጅጅጋ ከተማ ነው። ከአዲስ አበባ በስተ ምስራቅ 655 ኪ ሜ እና ከሐረር ደግሞ 130 ኪ ሜ ላይ የምትገኘው ጅጅጋ ከየክልሉ የሚመጡ እንግዶቿን ለማስተናገድ ዝግጅት የጀመረችው ከወር በፊት መሆኑ ታውቋል። የጸጥታ አጠባበቁ በተለይ በእጅጉ መጠናከሩም ተሰምቷል። ከዚሁ የተነሳ ኣንዳንድ የከተማይቱ ኗሪዎች ፍተሻው እና ወከባው በዝቶብናል ሲሉም ያማርራሉ። አንድ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የጅጅጋ ከተማ ኗሪ ደግሞ የተመቱ እና የተዘረፉም አሉ ይላሉ።

የክልሉ የማስታወቂያ እና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሐመድ ጎሬ ግን ይህ መሰረተ ቢስ አሉባልታ ነው ሲሉ አስተባብሏል።

የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ዘንድሮ በሶማሌ ክልል መከበሩ ያለምክኒያት ኣይደለም የሚሉ ወገኖችም ኣሉ። ምክኒያቱ ደግሞ በእነዚህ ወገኖች መግለጫ መሰረት በክልሉ ሁለት አስርተ ዓመታትን ያስቆጠረውን ኣለመረጋጋት መቆጣጠር የተሳነው የኢትዮጵያ መንግስት ጅጅጋ ላይ የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን በማክበር በክልሉ ሰላም የሰፈነ ኣስመስሎ ለፕሮፓጋንዳ ሊጠቀምበት ኣስቦ ነው።
የክልሉ መንግስት ቃል ዓቀባይ አቶ መሐመድ ጎሬ ግን ይህንን ኣይቀበሉትም።

ጸጥታን በተመለከተ መንግስት በአካባቢው ሰላም መስፈኑን ቢናገርም ሸማቂው የኦጋዴን ነጻ ኣውጪ ግንባር ONLF በበኩሉ በመንግስት ወታደሮች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት እየሰነዘረ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል። የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ መሐመድ ጎሬ እንዲያውም ONLF ብሎ ነገር የለም ካለም የሚገኘው በውጪ እንጂ በክልላችን ኣይደለም ባይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ለጥቆ በቆዳ ስፋቱ በሁለተኛነት የሚጠቀሰው የሶማሌ ክልል 400 ሺህ ስኩዌር ኪ,ሜ ኃህል ስፋትም አለው። የህዝብ ብዛቱ ከ5 እስከ 6 ሚሊየን ይገመታል። በረኃማነት ቢያጠቃውም ክልሉ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት እንዳለው ይታመናል።

ጂዓፈር ዓሊ

ሸዋዬ ለገሠ

dw.de

No comments:

Post a Comment