ነፃነት በምንም መንገድ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም!!
ገዢው ፓርቲ እና የፓርቲው ሎሌወች በተቆጣጠሩዋቸው ሚዲያዎች ልፍለፋቸውን ተያይዘዋል፡፡ ልፍለፋቸው ተመሳሳይና
አሰልቺ ነው፡፡ በቃ ሌላ የለም ይሄን ያህል ኪሎሜትር መንገድ ተጠናቀቀ፣ሊጠናቀቅ ነው፣20 በመቶ ተጠናቀቀ ምናምን
እያሉ ስሜት የማይሰጥ አሰልቺ ልፍለፋቸውን ተያይዘዋል፡፡ ከባቡሩ ግንባታ ጋርም ተያይዞ ትንሽ አከባቢ ኃዲድ
በመዘርጋት ለካሜራ ለማዋል እና የተለመደውን ፕሮፓጋንዳ ለመንዛት የቀደማቸው የለም፡፡ እነዚህ ሆድ አደር ጋዜጠኞች
መንግስት መንገድ መሰራትን እንደትልቅ ችሮታ ይቆጥሩታል፡፡ መንግስት መንገድን ጨምሮ የመሰረተ ልማትን ከህዝብ
በሚሰበሰብ ግብር እንደሚሰራ እንኳ ያላወቁ ሆድ አድር ናቸው፡፡ ሰውን ያህል ትልቅ ፍጥረት በሆዱ ማሰብ ከጀመረ
አደጋው ብዙ ነውና የጋዜጠኛ ተባዬዎቹ ተግባር የሚገርም አይደለም፡፡
እርግጥ ነው ልማትን የሚጠላ የለም፡፡ ልማት አንዱን እየጎዳ ሌላውን እየጠቀመ ሲሄድ ግን ልማትነቱን ይጠፋና
ሌላ ስያሜ ይይዛል፡፡ እንደማስበው ልማት ማለት መንገድ ልሰራልህ ነውና በቶሎ ንብረትህን አንስተህ ጥፋ ማለት ለኔ
ልማት አይደለም፡፡ የልማት ቀጥተኛ ትርጉሙ ማልማት፣ማሳደግ ነውና፡፡ ከዚህ ገር ተያይዞ በርካቶች በልማት ስም ቤት
ንብታቸው በተኙበት ፈርሷል፡፡ በአንባገነኖቹ በኩል ለዚህ መልሱ ለልማት ነው የሚል ነው፡፡ ይሄ ‹‹ልማታዊ
መንግስት›› ነኝ የሚል ልፍለፋቸውም ልማትን አስቀድማለሁ የሚል ነው፡፡ በዜጎች ቀጥተኛ ተሳፎ ያልተካሄደ ልማት
ልማት ሊባልም አይችልም፡፡ ምክንያቱም ልማቱ ለዜጎች እስከተሰራ ድረስ ሁሉም ዜጋ ተሳታፊ ሊሆን ይገባል፡፡ እኔ
አውቅልሃለሁ የትም አያደርስም፡፡ ልማት እየሰራሁ ስለሆነ የመብት ጥያቄ መጠየቅ አትችልም የሚባል ነገር የለም፡፡
አሁን በአዲስ አበባ እየተሰራ ያለውን የከተማ ባቡር መስመር ዝርጋታ እንዲሁም የአስፋልት ማንጠፍን አስመልክቶ
በርካታ ነገሮችን እየሰማን እንገኛለን፡፡ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ወራሪውን ጣልያንን አጥንታቸውን ከስክሰው ውድ
ሕይወታቸውን ሰውተው ወደመጣበት የመለሱት ነፃነታቸውን ስላስቀደሙ ነው፡፡ ነፃነት ከሁሉም ላቀ ነገር ነውና፡፡
ለመንገድና ለድልድይ ከሆናማ ጣልያንን የሚያክል ማን አለ? ይህም አሁን ድረስ አገልግሎት እሰጡ ያሉ በጥራታቸው
መንገዶቹ ምስክር ናቸው፡፡ ምን ዋጋ አለው ይህ ብቻውን፤ ያለነፃት ምንም ወጋ እንደሌለው አባቶቻችን ጠንቅቀው
አውቀዋል፡፡ አሁን በዚህ ዘመን ያለን የተማረውም ሆነ የተማረ የሚመስለው ከአባቶቹ በተሻለ የቴክኖሎጂ ዘመን እኖረ
ከቀደምት አባቶቹ እኩሌታ እንኳ የማሰብ ደረጃ ላይ አለመገኘቱ አሳዛኝም አሳፋሪም ነው፡፡
የባቡር ዝርጋታውን ተከትሎም እየሰማን ያለነው አጀብ የሚያሰኝ ነው፡፡ አንድ ኪሎ ሜትር እንኳ ሃዲድ ሳያነጥፉ
ለፕሮፓጋንዳ መሮጥ ምን የሚባል ነው? አንባገነን ገዢዎችና የጦርነት ስሜት ያልተላቀቃቸው አገዛዞች ሁል ግዜ
የቀደመውን ታሪክ በማጥፋት ለነሱ እንዲፃፍላቸው ይፈልጋሉ፡፡ የባቡር ትራንስፖርትም ቢሆን ለኢትዮጵያውያን አዲስ
ነገር አይደለም፡፡ ከጅቡቱ ድሬዳዋ-አዲስ አበባ የተዘረጋ የባቡር መንገድ ነበር፡፡ መቼም መንገዶቹን
ጣልያኖች፣የባቡር ዝርጋታውን ፈረንሳዮች መስራታቸውና ያሁሆቹ በሚጠየቁት ዋጋ ልክ በለብለብ የሚሰሩት ቻይናዎች
መሆናቸው ነገሩ አዲስ አለመሆኑን እና አደግን ተመነደግን የሚባለውም ጥቂቶችን ወደላይ በማውጣት በርካቶችን ለስደትና
ለከፋ ችግር እየዳረገ መሆኑ እየታወቀ ይህን ያህል ቀረርቶና ፉከራው ለምን እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡
ከማቴሪያል በዘለለ ግን ነፃነታችንን እንደምንፈልግ ገዢዎቻችን ሊገባቸው አልቻለም፡፡ አልያም እንዲገባቸው
አልፈለጉም፡፡ ይህን ከመገንዘብ እና ለዜጎች ጥያቄ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ የህፃን ጫወታ ተያይዘዋል፡፡
በዚህ ዘመን ያሉ ገዢዎቻችን አንደህፃን እያታለሉ ይገኛሉ፡፡ በእውነቱ ይህ ለዚህ ዘመን የማይመጥን ነው፡፡ አገርን
እመራለሁ የሚል ስርዐት እታች ወርዶ እንደህፃን ሊያሞኘን ሲፈልግ ማየት የሚያሳዝን ነው፡፡ ነፃነታችን ነፃነታችን
ነው፡፡ በሱ ድርድር ማድረግ አንፈልግም፡፡ አርግጥ ነው ቀደምት አባቶቻችን የውጭ ወራሪዎችን በታላቅ ቆራጥነት
በመመከት የሚከበር ታሪክ ፅፈው አልፈዋል፡፡ የነፃነት ትግሉ ግን አሁንም አልቆመም፡፡ ልዩነቱ የፊቶቹ የውጭ
ወራሪዎች እና ቅኝ ግዛት ፈላጊዎች ሲሆኑ፤ የአሁኖቹ ደግሞ ዘመናዊውን ቅኝግዛት የሚያካሂዱ ከፋፋዮችና አምባገነኖች
ናቸው፡፡ እነዚህ ከፋፋዮችና አምባገነኖች ናቸው እንግዲህ ልማት ልናለማ ነውና የመብት ጥያቅ አትጠይቁ እያሉ የሞኝ
ቀልድ የሚቀልዱት፡፡ ነፃነት ግን ከባቡር መንገድ በላይ ነው፡፡ ነፃነት ከበድን ህንፃ በላይ ነው፡፡ ሰዎች
የፈቀዱትን ለማድረግ ነፃነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህም በምንም መንገድ ለድርድር የሚያቀርቡት አይደለም፡፡
Grace Abate
http://freedom4ethiopian.wordpress.com/2013/11/09/345-12/
No comments:
Post a Comment