ወሬ ነጋሪው
መጽሐፍ ወሬ ነጋሪ
ደራሲ መሐመድ ይማም
ግምገማ በልጅግ ዓሊ
በሚያዚያ ወር የሰሜን አሜሪካ ክረምት ገና ሙሉ በሙሉ ሳይለቅ በፊላደልፊያ ከተማ ውስጥ በማይታወቅ ሰው
ኢትዮጵያዊቷ ጀግና ተገደለች። በምሳ ሰዓት አካባቢ ወደ ቤት የተመለሰችው እህቷ ጠዋት በሰላም የተለየቻትን በደም
አበላ ውስጥ ተዘፍቃ አገኘቻት። ፖሊስም ጠራች። የፍላደልፊያ ፖሊስ ይህንን የተቀነባበረ ግድያ የፈጸመውን ወንጀለኛ
መያዝ ስላቃተው እንቆቅልሹ ያልተፈታ በሚል መዝገቡን ዘጋ።
ይህች ጀግና ሴት በአንድ ወቅት አንድን ትውልድ ያንቀሳቀሰ ትግል ውስጥ የጎላ ሚና ነበራት ። ታሪኳ ሲተረክ
የጅግኖች ጀግና፣ የኢትዮጵያውያን ሴቶችን ሁሉ የሚያኳራ ተግባር እንዳከናወነች እንኳን ወዳጆቿ ጠላቶቿም ቢሆኑ
አይክዱትም። ከአዲስ አበባ እስከ አሲምባ በተለያዩ የሚፈትኑ ተግባሮች ለቆመችለት ዓላማ ታማኝ ሆና፣ የኢትዮጵያን
ሕዝብ በማስቀደም፣ ለግል ጥቅሟ ሳትቆም፣ አለ አንዳች ፍርሃት ተወጥታዋለች።
በዚያ ቀውጢ ሰዓት በቀይ ሽብር ወቅት በኢሕአፓ ውስጥ ከማደራጀት ሥራዋ ሌላ በወቅቱ ተወዳጅ የነበረችው የጎህ
መጽሄት ዋና አዘጋጅ ነበረች። ይህች እህት የፈጸመችውን ገድሎች ሁሉ በጽሁፍ ለማቅረብ ዱካዋን በጥልቀት መመርመር
ያስፈልጋል። ዛሬ በሃገራችን ለነጻነትን ለመብት በተደረገው ትግል ውስጥ እንደተሰውት ዜጎችየእሷም ስም በወርቅ ቀለም
ተጽፎ ይገኛል።
መዝገብነሽ አቦዬ ሲዳሞው ውስጥ የተሰዋው የኢሕአፓ ብርቅዬ የሌላው ጅግና የብርሃኑ እጅጉ ባለቤትና የአንድ ልጅ እናት ነበረች።
“የእሷ መሞት ነው ሕይወት አጭር መሆኗን አስረድቶኝ ይህንን “ Wore Negari’’ ወሬ ነጋሪ’ የተባለውን
መጽሐፍ ከማውቀውና ከሰማኋቸው ያሰባሰብኩትን ጨምሬ ለመጻፍ ያነሳሳኝ’’ ይላል መሐመድ ይማም የ“Wore
Negari’’ ደራሲ። እውነትም ነው ይህች ጀግና የስነ ጽሁፍ ጠበብት ለትውልድ የሚጠቅም ታሪክ እንደያዘች በጩቤ
ተዘክዝካ ተገድላለች። እውነት ነው ከምትወዳት ልጇ ጋር ሳትገናኝ አድብቶ በጠበቀ ጠላት ባልተዘጋጀችበት ወቅት
ተጠቅታለች። እውነት ነው ያ ጓዶቿን የጨረሰውን አረመኔ መንግሥት መጨረሻ ሳታይ ተቀድማለች።
መሐመድ ይማም ወደ ተማሪዎች ትግል ከዛም ወደ ኢሕአፓ እንዴት እንደገባ በመጽሐፉ ላይ አስፍሮታል። እንዴት ወደ
ጎህ ጋዜጣ አዘጋጅነት እንደተላለፈ አሳውቆናል። በቀይ ሽብር ወቅትም የደረሰበትን ፈተና ለመግለጽ ሞክሯል። ይህንን
ለወሬ ነጋሪ ከተረፈው ግለሰብ የቀረበልንን ትረካ ማመን አስቸጋሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። በተለይ በቀይ ሽብር ወቅት
የተፈጸመውን።
መሐመድ ይማም ለወሬ ነጋሪ የተረፈው ተአምራዊ በሆነ ሊታመን በማይቻል ሁኔታ ከእስር ቤት በማምለጤ ነው
ይለናል። የሰጠን አምንክዮ ግን አንባቢያንን ሊያሳምን የሚችል ሆኖ አላገኘሁትም። መሐመድ ፒያሳ ከሚገኘው በወቅቱ
ሐጂ በመባል የሚታወቀው አረመኔ ከሚያስተዳድረው እስር ቤት ውስጥ አለ እንዳች ቅድሚያ ስምምነት ለማምለጥ መቻሉን
ለማመን እንቸገር ይሆናል። ለመሆኑ ሐጂ ማነው?
ሐጂ በቀይ ሽብር ወቅት ፒያሳንና አካባቢውን ያንቀጠቀጠ፣ ብዙ ወጣቶችን እንደገደለ የሚታወቅ አረመኔ ነበር።
ሐጂ ከሰራቸው አሰቃቂ ተግባሮች ውስጥ የሚጠቀሰው አንድ ቀን ፒያሳ ላይ ከአብዮት ጥበቃዎች ጋር ሲዞር አንድ ራቁቱን
የሚሄድ እብድ እየፈሩ ሰዎች ሲሸሹ ይደርሳል። እብዱን ሁለተኛ እዚህ ሰፈር እንዳትደርስ በማለት ጥይት ተኩሶ
አስፈራርቶ ያባርረዋል። በሌላ ቀን ሐጂ በመኪና ሲሄድ እብዱን እዛው አካባቢ ያገኘዋል። እብዱ ትዕዛዙን ባለመስማቱ
ተናዶ “እብድና እባብ ጭንቅላቱን ካልመቱት አይሞትም’’ በማለት በጥይት መትቶ ይገድለዋል። ይህ ተግባር አዲስ
አበባ ውስጥ ተፈጸሙ ከተባሉት ሁሉ ግፎች ሁሉ ገዝፎ የታየበት ወቅት ነበር።
አረመኔው ሐጂ የፓርቲው የዞናል ኮሚቴ(በወቅቱ ትልቅ ስልጣን የነበረ) አባልና የጎሕ መጽሄት አዘጋጅ ለሆነው
መሐመድ ይማም ሃዘኔታ ተሰምቶት ምንም ዓይነት ግርፋትና ሥቃይ ሳያደርስበት፣ እንዲያጋልጥም ሳያስገድደው መቅረቱ ነው
አመኔታ እንድነፍገው ያስገደደኝ። ትርክቱ ቀጥሎ ሐጂ መሐመድ የነገረውን ሁሉ አምኖ ወደ እስር ቤቱ ምንም
ሳያደርስበት ተመለሰ። ከሁለት ሳምንት በኋላም ከእስረኞች ጋር ተቀላቅሎ በአንድ አብዮት ጥበቃ ብቻ ታጅበው ሽርሽር
ወጡ ። በዛው ግን አልተመለሰም። ቀስ ብሎ አብዮት ጥበቃው ለሌሎቹ መሣሪያውን ሲያሳይ መሐመድ ከእስር ቤት አምልጦ
ወደ ተክለሐይማኖት ነጎደ። ማመን ወይም አለማመን?!!!! እዚህ ላይ ነው ጥርጠሬን የሚጭረው። ለመሆኑ በቀይ ሽብር
ወቅት እንደ መሐመድ ዓይነት ከፍተኛ የፓርቲው አባላት እንዲህ በቀላሉ ነበር እንዴ የሚመረመሩት? እኔ እስከማውቀው
ድረስ፣ እስከ አሁንም ከተጻፉት መጽሐፍት እንደተረዳነው ምርመራው የከበደና የጠለቀ ነበር። የመጨረሻው ቀይ
ሽብር(ከዛም በኋላ ተደርጎ ይሆናል) እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር 1976 ከመሐመድ ያነሰ ስልጣን በነበራቸው ላይ
መካሄዱን በቅርብ ከተጻፉት መጽሐፍት ተረድተናል። መሐመድ ይማም ይህንን ሁኔታ በመጽሐፉ ላይ ታአማኒነት ባለው መልክ
አላስረዳንም።
ይህንን አፈ ታሪክ እንኳን በቀይ ሽብር የነበረ ሰው ወይም ስለቀይ ሽብር የሰማ የሰሞኑም ሕጻን አያምነውም።
የማይታመን ድርጊት እመኑ ሲለን ግን የሚታመን ዕውነታ እየሸሸገን ይመስላል። መሐመድ ይማም የታሰረበትን ሁኔታ
ሲተርክ ባጭሩ እንዲህ ይላል፡ -
ቀይ ሽብር በተጧጧፈበት ወቅት መሄጃ ስላልነበራቸው ፒያሳ አካባቢ ከሚገኝ አንድ የቤት ቁሳቁስ መሸጫ ውስጥ
አምስት ሆነው ለማደር ይስማማሉ። በወቅቱ አስሳ ስለነበር ምንአልባት አብዮት ጥበቃዎች ቢመጡ መሸሻ መንገዳቸውን
ተነጋግረው መሣሪያ ይከፋፈላሉ። በዚህ ወቅት ደራሲው መሣሪያ እንደማይፈልግ ግልጽ ያደርጋል። እንደጠረጠሩት ከተኙ
በኋላ አብዮት ጥበቃዎች መጥተው ያንኳኳሉ። አምስቱም ተነስተው ዝግጅት ያደርጋሉ። መሸሽ ሲጀምሩ ከመካከላቸው
አንደኛው ቦንብ ጥሎ አንዱን አብዮት ጥበቃ ይገድላል። ከአምስቱ ሁለቱ ሊያመልጡ ሲሞክሩ ይገደላሉ።በዚህ ወቅት
አንዱ ሆዱ ላይ ተመትቶ ስለነበር ብዙ ይደማ ነበር። ቦንቡን የጣለውን ዛፍ ላይ ተደብቆ አግኝተው አብዮት ጥበቃዎቹ
ይገድሉታል። ደራሲው ከተደበቀበት ቦታ ይያዛል። ወደ መኪና ሲወስዱት ሆዱን የተመታውን ተይዞ ያገኘዋል። እሱም
ደራሲው ከእነርሱ ጋር መሆኑን ያጋልጣል። ይህ የቆሰለው ወጣት እዛው ቀይ ሽብር ይወሰድበታል። በእንደዚህ አይነት
ከአምስቱ ደራሲው ብቻ ለወሬ ነጋሪ ይተርፋል። ከዚህ በኋላ ደራሲው በጣም በመፍራቱ ምክንያት የሆነውን ብዙም
አያሳታውስም። ከሦስት ቀን በኋላ ነፍስ ያውቃል። ምንም ጉዳት እንዳላደረሰና በማንኛውም ጉዳይ አብዮቱን እንደሚቀበል
ይናገርና ካለ ስየል(ቶርቸር) ፣ ካለ ቃለ መጠይቅ ይድናል። . . .
ይህንን አፈ ታሪክ ለማመን ይከብዳል። ወቅቱ ምን እንደነበር ለሚያውቅ ሰው የመሐመድ ይማም ከማስገረም አልፎ
የደበቀው ጉዳይ እንዳለ መጠርጠሩ አይቀርም። “የአንድ ጓድ ነፍስ በሺህ አናርኪስቶች ደም ትለወጣለች’’ ተብሎ
በሚፎከርበትና በተግባር በሚፈጸምበት ወቅት፣ አንድ ሰው የኢሕአፓን ወረቀት ይዘሃል ተብሎ በሚገደልበት ወቅት፣
መሐመድ ይማም የፓርቲው ዞናል ኮሚቴ አባል የጎሕ መጽሄት አዘጋጅ፣ መሣሪያ ከታጠቁ ግለሰቦች ጋር አብሮ የነበረ፣
መሣሪያውን በመጠቀም አንድ አብዮት ጥበቃ ከገደሉት ውስጥ አንዱ፣ ሳይገረፍ፣ ሳይጠቁም፣ መዋቅሩን ሳያጋልጥ፣ ሌሎችን
አሲይዞ ሳያስገድል በነጻ “በቃ ተወው የኔ ልጅ ደግ አደረክ። ሌላ ቀን አይልመድህ’’ ተባልኩ ብሎ አፈ ታሪክ
ሲተርክ የሚያምን ካለ የሐጂንና የሌሎቹን የሕይወት ታሪክ የማያውቅ ብቻ ነው። ይህ የመሐመድ አፈ ታሪክ ለማመን
ያዳግታል። ማመን ብቻ ሳይሆን በዚህ ጽሁፍ ሊደበቅ የሚሞከር ሌላ እውነት እንዳለ እየጎላ ይታይበታል።
ከዚህ በማያያዝ መሐመድ አደገኛ እስረኛ ከሚባሉት ውስጥ ሳይቆጠር ከሌሎቹ እስረኞች እንደነበር ስንሰማ መሐመድ
ለነ ሐጂ ከሚገባው በላይ ታማኝ እንደነበረ መጠርጠራችን አይቀርም። በተለይ መሐመድ እንዴት ከእስር ቤት እንዳመለጠ
ሲተርክ በአንድ አብዮት ጥበቃ ለሽርሽር ከወጡ በኋላ እንደው ሳይሮጥ ቀስ ብሎ በመዝናናት መጥፋቱን እንድናመነው
ያደረገው ሙከራ የሚገርም ቴያትር ነው። ጥሩ ልብ ወለድ ይመስላል። ማምለጡንስ ያምልጥ እንመን ከዛ በኋላ ለመደበቅ
የሄደበት ቦታ ሁሉ ከእሱ ከመታሰሩ በፊት ተጋልጠው የነበሩ ቦታዎች ሲሆን ምንም አደጋ ሳይደርስበት በነጻው ዓለም
ሲንደላቀቅ እንደነበረ ነው የሚጽፈው። የጠቀሳቸውን ቦታዎች ለምናውቅ ሰዎች ያስደምመናል። ሲኒማ ራስና አደሬ ሰፈር
እንኳን በቀይ ሽብር ወቅት ከዛም በኋላ የማይደፈር ነበር።
ከዚህ ተነስተን ሙሉ የመጽሐፉን ይዘት ስንመረምረው መሐመድ በግል የሚረብሽውን ጉዳይ በውሽት ብዛት ለመወጣት
የሚደርገው ጥረት እንዳለ መረዳት አያዳግትም። ቀን ይጠብቃል እንጂ ለወሬ ነጋሪ እኔ ብቻ ተረፍኩ እንዳለው
እንደማይሆን እርግጠኛ መሆን ይቻላል። ሌላ የውስጡን የሚያውቅ ብቅ ሊል ይችላል። በተለይ እሱ በመጥፋቱ ምክንያት
የተገደሉት አሥራ አንድ የኢሕአፓ አባላት እንዴትና ለምን እንደተገደሉ የተሰጠ ማብራሪያ የለም። ይህም ቢሆን ወደፊት
ታሪኩ መጻፍ ይኖርበታል። የቴያትሩ መጋረጅ ተዘግቶ እውነተኛው ታሪክ እንዲገለጥ በገጉት እንጠብቃለን።
ከመጽሐፉ አንድ ትልቅ ቁም ነገር አገኘሁበት። እንዲህ ይላል፡ -
Nothing happened to me that day. It was the longest day of my life. I
was completely shook up. I was terror stricken. I remember some of the
prisoners saying I must not be the leader in the organisation. Since I
was so scared. And scared I was.
መሐመድ የሚለን በጣም ፈርቼ መርበትበቴን ያዩ ሌሎች እስረኞች የድርጅቱ መሪ ልትሆን አትችልም አሉኝ ነው።
እስረኞቹ ስንት ጀግና በተመለከቱበት እስር ቤት ከፍርሃት የተነሳ ሽንት ቤት ይሆን፣ እስር ቤት፣ የማይለይን ሰው
እንደ ድርጅት መሪ መቀበል ቢያቅታቸው የሚገርም አይሆንም። እኔም መጽሐፉን አንብቤ ከጨረስኩ በኋላ የተሰማኝ ይህንኑ
ነው። እውን መሐመድ የፓርቲው አባል ነበር? የሚለው ጥያቄ ነው ጭንቅላቴ ውስጥ የተመላለሰው። በዚህ ዓይነት
ፍርሃት ስንት ሰው አጋልጦ በቀይ ሽብር እንዲመቱ አድርጓል? ከእነዚህ ውስጥ ስንቶቹ ናቸው ንጹሐን? መሐመድ በሌላ
መጽሐፍ ይገልጽልን ይሆን? እጠራጠራለሁ።
መሐመድ ይህ ሁሉ ጥፋት የኢሕአፓ ነበር ብሎ ለማሳመን የደረገውን ጥረት የሚገርም ነው። ይህ አቋሙ የአሁን
ይሁን የዛን ጊዜ ለማመን ያዳግታል። ይህ ሁሉ ተቃውሞ በፓርቲው ላይ ከነበረው ለምን ከእነ ብርሃነ መስቀልና ከነ
ጌታቸው ማሩ ጋር አልሆነም? መንገዱ ጠፍቶት ይሆን? ይህም በመጽሐፉ ውስጥ መልስ ተፈልጎ የማይገኝበት ነው።
በእንደሱ ዓይነት ትልቅ የፓርቲ ስልጣን ላይ ነበርኩ ያለ ጥፋቱን ካልተቀበለ ማነው ጥፋተኛ ታዲያ? ከነበረው ኮሚቴ
ለወሬ ነጋሪ የቀረው እሱ ብቻ ስለሆነ እንደፈለገ ሁኔታው ቢያጣምመው የሚያስተካከል እንደሌለ መሐመድ የገመተ
ይመስላል። መሐመድ ይህንን መጽሐፍ ሲጽፍ በወቅቱ ከእሱ ጋር በኮሚቴ የሠሩ ባይኖሩም ከጠቅላላው ሁኔታ ተነስተን
የመሐመድን ሕይወት ያተረፈው ምን እንደሆነ መገመት አያዳግተንም። መሐመድም የዛን ትውልድ አባላት ችሎታ የሚፈታተን
ጥያቄ እንዳላነሳ ሊረዳው ይገባል።
ለማጠቃለል ያህል መዝገብነሽ ፍላደልፊያ ከመሞቷ በፊት ደራሲው ስልክ ደውላ አንድ ሰው በባቡር ፍላደልፊያ
መግባቱን ነግራኝ ነበር፣ ስትነግረኝም ጭንቀት ነበረባት ይላል። ለመሆኑ ያ ሰው ማነው? ይህንን ጉዳይ ለፖሊስ
አስታውቆ ነበር? ካላስታወቀስ የመዝገብነሽ ገዳይ እስከ አሁን ነጻ የሆነው በዚህ ምክንያት ቢሆን ኅሊናው እንዴት
ይቀበለዋል? መሐመድ ይህንንም በሚመለከት ስለ መዝገብነሽ ሞት የተደበቀውን እንቆቅልሽ ይፈታው ይሆን? ስለ
መዝገብነሽ ሞት የሰጣቸው ግምቶች ዛሬ በመጽሐፉ ውስጥ ሊያስተባብል ከሚሞክረው ታሪክ ጋር የተያያዘ ይሆን? እውነት
ለመናገር የሚፈራው ጉዳይ ይኖር ይሆን?
መጽሐፉ ብዙ ጥያቄዎች ፈጥሮ አልፋል እንጂ መልስ የለውም። ሐቁን ከሌሎች እናነብ ይሆናል። መሐመድም ድፍረት አግኝቶ፣ ከፍርሃቱ ተላቆ እውነቱን ያስረዳን ይሆናል። ማን ያውቃል?
ስለ ሕዝብ ትግል ሲሉ ስለተሰዉ የሚያስቡ ሁሉ በሰላም ይክረሙ ።
በልጅግ ዓሊ
zehabesha
No comments:
Post a Comment