ሙርሲ ከስልጣን የተወገዱ ጊዜ አንድ ዜና በጨዋታ ለጥፌ ነበር፡፡ የዜና በጨዋታዋ አላማ፤ ወሬውን ከማድረስ
በተጨማሪ ሁለት ነገር ነበር፡፡ አንደኛው፤ ህዝብ ግር ብሎ ከተነሳ የሚሳነው ነገር እንደሌለ ለሚሰማን መንገር፣
ሁለተኛው ደግሞ የእኛዎቹ ፌደራል ፖሊሶች እና አጋዚ ወታደሮች እንኳንስ እንዲህ ጫን ያለ ነገር መጥቶ ይቅርና
እንዲሁም እንዲሁ ናቸው የሚለውን ለሚመለከት ሰው ለማመላከት እና መልዕክት ለሚያደርስ ሰው ልቦና ግዙ… ተብላችኋል
ብሎ ያደርስልን ዘንድ መንገር ነበር፡፡
(በነገራችን ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ እኮ “ሙደኛ” ነው፡፡ በተለይ በ97ቱ ጊዜ እንዳየነው ህዝቡ እምቢኝ ካለ
ፖሊሶቻችን ከጎናችን መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ ይሄንን ገዢው ፓርቲም ያወቃል፡፡ ምነው እንኳ ያኔ ራሱ እኮ
የተሰጣቸው አንድ ክላሽ ከአንድ ጥይት ጋር ብቻ ነበር፡፡ “ይቺን ምን እንድናደርጋት ነው” ብሎ አንዱ ፖሊስ ሲጠይቅ
አይደለም እንዴ “ለሚስኮል አንድ ጥይት መች አነሳህ…” የተባለው…!)
ወደ ነገራችን ስንመለስ… አንድ ወዳጄ “ሙርሲ በህዝቡ ከይሲ በወታደሩ ሂድ ከዚ ተባሉ” የሚለው የዜና በጨዋታ
ርእሴን እንዳልወደዱት ሲነግሩኝ፤ “አረ አቤ… ነገሮችን ስትገልጽ ለሰው ሞራል ተጠንቀቅ…” ብለውኝ ነበር፡፡
አልገባኝም ወዳጄ… ለማን ሞራል ነው የምጠነቀቀው… መቼም ለሙርሲ ሞራል ተጠንቀቅ አይሉኝም… እንዲህ ያልኩት ሙርሲን
ጠልቼ ወይም ንቄ አይደለም፡፡ ነገር ግን ሙርሲ የእኔን አማርኛ አያነቡም፡፡ እንዴት አያነቡም… ትላለህ… ብሎ
የሚቆጣ ካለ ምክንያቱም ሰውዬውን ወታደሮቹ እስር ቤት ጨምረዋቸዋልና ነው፡፡
የሚስቅ ስቆ የሚበሳጭ ተበሳጭቶ ካበቃ፤ አሁን ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባለን፡፡ የግብጽ ወታደር የመንግስት
ግልበጣ ነው ያደረገው… ወይስ ሃላፊነቱን ነው የተወጣው…!? እነሆ ዋናዋ ጥያቄ ተጠየቀች… ብለን አዲስ መስመር ላይ
ተመቻችተን እናውራ፤
እንደኔ እምነት የግብፅ ወታደር ኩዴታ ፈፅሟል የሚያስብል ነገር አላየሁም፡፡ በርካታ ህዝብ አደባባይ ወጣ
ተቃውሞውንም አሰማ፡፡ (አንዳንድ ወዳጆቼ፤ “ጥቂት ግብጻዊያን ስለጮሁ እንዴት ህዝብ ትላለህ?” ብለውኝ ነበር፡፡
እነዚህ ሰዎች ኢቲቪ የሚሰሩ መሆን አለባቸው፡፡ እነ ኢቲቪ በናታችሁ የጥቂት ብዛቱ ስንት ነው….!? ይሄንን ጥያቄ
ስንት ጊዜ ጠየቅን… ዜና አንባቢውም ዝም ቲቪውም ዝም ሆነብን እንጂ…) ሀቂቃውን ለመናገር ግን በግብጽ ተቃውሞ
የወጡት ብዙሃን አንደነበሩ እድሜ ለቴክኖሎጂ በወቅቱ በቦታው ተገኝተው ሲዘግቡ የነበሩቱ ቀጥታ ሲያነፃጽሩልን
ነበርና፤ “ሙርሲ ይሂዱልን ከዚ…” ያሉት ብዙ እንደነበሩ ድንጋይ ነክሰን ብንምልም አንፈራም፡፡ ስለዚህ በእኔ
በምስኪኑ እምነት የእነዚህ ብዙሃን አቤቱታ መሰማት አለበት፡፡ ለዚህም ወታደሩ ያደረገው መፈንቅለ መንግስት ሳይሆን
አፍቅሮተ ህዝብ ነው ባይ ነኝ፡፡ (ለብዙሃኑ ጆሮ ሰትቷልና!)
እርግጥ ነው ሙርሲ ከዚህ በፊት ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ተመርጠው ነው ወደ ስልጣን የመጡት፡፡ እና ቢሆንሳ
“ተመረጥኩኝ ብለሽ አትበይ ደንበር ገተር… ከልተመቸው “ንኪው” ይልሻል ባላገር…” የሚል ዘፈን አለ አይደል
እንዴ…! (ከሌለም እኛው እናስነካዋለን!) የምሬን ነው፡፡ ማንም ቢሆን ገና ለገና በምርጫ ነው የመጣሁት ብሎ
በስልጣኑ ላይ መዘናጋት፣ መዝናናት ወይም ማዛጋት ቢያሳይ መራጩ ህዝብ ወግድ ሊልም መብቱ አለው፡፡ (ብዙሃን ይመውዕ
ይላል መጽሀፉ) እርግጥ ነው እዚህ ጋ አንድ ነገር እረዳለሁ፡፡ መራጩ መብት እንዳለው ሁሉ ተመራጩም
የተመረጥኩበትን ጊዜ ሳልጨርስ አልወርድም ብሎ “የመገገም” መብት አለው፡፡ ጋሽ ሙርሲም ያደረጉት ይህንኑ ነበር፡፡
ውጥረትም
የነገሰው በዚህ የተነሳ ነበር፡፡ ይሄኔ ነው የሆነ አካል ጣልቃ ገብነት የሚያስፈልገው፡፡ ለዚህም ነው ወታደሩ ጣልቃ የገባው፡፡
እንግዲህ ይህንን እኔ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ስለው ሌሎች ደግሞ ይሄማ መፈንቅለ መንግስት ነው ይላሉ፡፡ ታድያ ምን ችግር አለው…? እኔም ያልኩትን ልበል ሌሎችም ያሉትን ይበሉ፡፡
አሁን ከሙርሲ እና ሌሎች ባለስልጣናት ወደ ማረፊያ ቤት መውረድ በኋላ ተቃዋሚዎቹ የልባቸው ደርሶ ወደ ጎጇቸው ሲመለሱ የሙርሲ ደጋፊዎች ደግሞ “ይቺን ይወዳል የሙርሲ ልጅ” ብለው “እየቀወጡት” ይገኛሉ፡፡
ይህ ሊመጣ እንደሚችል ተንታኞቹ ድሮውንም ገምተዋል፡፡ ማለቂያው ምን ሊሆን እንደሚችል ግን የሚያውቀው የላይኛው ብቻ ነው፡፡
እኔ ይቺን እየተየብኩ ባለበት ሰዓት የወታደሩን ጣልቃ ገብነት በመቃወም በተቀሰቀሰው አዲሱ ተቃውሞ ህይወታቸውን
ያጡ ሰዎች ቁጥር ሃያ ሊደርስ እየተንደረደረ ነበር፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡ እነዚህ ተቃዋሚዎች እየጠየቁ ያለው ጥያቄ
ትክክል ነው፡፡ “ድምጻችን የት ነው…! የመረጥነውን ሰውዬ የት አደረሳችሁት…!” እያሉ ይገኛሉ፡፡ ይሄ እጅግ
በጣም ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡
መጨረሻ ላይ እንደኔ አስቴየት ያኛውም ትክክል ይሄኛውም ትክክል ሆነ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ዲሞክራሲ አጣብቂኝ ውስጥ የምትገባው ይሄኔ ሳይሆን አይቀርም፡፡ (የሚል ሌላ አስተያየት ልጨምራ!)
ለማንኛውም በቅርቡ ኢትዮጵያውንን ርስ በርስ ብናበጣብታቸውስ… ብለው ሲዶልቱ ያየናቸው ሙርሲ እና
ባለስልታኖቻቸው አሁን ለራሳቸው ብጥብጥ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ለማንኛውም በቅርቡ ዜጎቻችንን ያለ አጥጋቢ ምክንያት
መድረሻ ያሳጡት ግብፆች አሁን ርስ በርሳቸው እየተጣሉ መድረሻ ተቸግረዋል፡፡
እውነቱን ተናገር ካሉኝ ደስ አላለኝም፡፡ መጽሀፉ የጠሉህንም ውደድ ይለን የለ… ስለዚህ የግብጽ ህዝብን ባለቤቱ ይታደገው፡፡ እላለሁ!
በባለፈው ዜና በጨዋታ የተቀየሙኝ ወዳጄን ግን የምጠይቃቸው ጥያቄ አለኝ፤ ሀገራችን ስንት ጉድ እያለብን፤
እንዴት በግብጽ ጉዳይ እንጣላለን…! የግድ መጣላት ካለብንስ በሀገራችን ምርት ብንጣላ አይሻልምን…! (ዋጋውም ቀነስ
ይላልናል)
source.....https://www.abetokichaw.com
No comments:
Post a Comment