(አርአያ ጌታቸው)
በአባይ
ወንዝ ዙሪያ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል በተነሳው አለመግባባት ዙሪያ ብዙዎች ብዙ ሲሉ አድምጠናል፡፡ በተለይ ደግሞ
ከተቃዋሚ ፓርቲዎች መንደር የተደመጠው ምላሽ ዛሬም ድረስ ብዙዎችን እያነጋገረ ይገኛል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ
የሀገሪቷ የፖለቲካም ይሁን የሌሎች ዘርፍ ምሁራን በጉዳዩ ዙሪያ ምንም ሲሉ አልተደመጡም፡፡ ይሄንን ነገር ሳብላላ
አንድ ሰው በአምሮዬ ብቅ አሉ፡፡ አልተሳሳቱም በፎቶው ላይ የሚመለከቷቸው ዶክተር መረራ ጉዲና፡፡
ዶክተር መረራን በአባይ ዙሪያ ማነጋገር የመረጥኩት አንድም
የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር በመሆናቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር በመሆናቸው ከእርሳቸው
ይበልጥ ጉዳዩን በሁለት አቅጣጫ የሚያይልኝ ሰው አይኖርም የሚል ድምዳሜ ላይ በመድረሴ ነው፡፡
እናም ዶክተር መረራን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ስድስት ኪሎ ወይንም ወደ ዋናው ግቢ አመራሁ፤ አገኘኋቸውም፡፡ ከየት እንደመጣሁ በመንገርም ቀጠሮ እንዲሰጡኝ
ጠየኳቸው፡፡ ዶክተር መረራ ለአዲስ ዘመን ያላቸውን አስተያየት ከገለጹልኝ በኋላ “የምነግርህን ቆርጠህ እንዳታወጣ”
ከሚል የግል ማሳሰቢያ ያዘለ አስተያየት ጋር ከእዚህ ቀጥሎ እንደ ወረደ ያቀረብነውን ማብራሪያ ሰጡኝ፡፡ ዶክተር
መረራ በጣም ከተጣበበው ጊዜያቸው ላይ ቀንሰው ለሰጡኝ የ55 ደቂቃ ቃለ መጠይቅም በእርስዎ በአንባቢዬ ስም
አመሰግናቸዋለሁ፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- እስኪ በሰሞኑ በአባይ ዙሪያ እየተባለ ስላለው ጉዳይ እርስዎ እንደ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር መረራ፡-አባይን የመጠቀም ጉዳይ
የኢትዮጵያ ሕዝብ መብት ነው፡፡ ነገር ግን እጠቀማለሁ ስትል እኔ እንደ ፖለቲካል ሳይንስ ምሁር የምለው መጎዳት
የለብንም ነው፡፡ ሊያነጋግረን የሚገባውም ይሄ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ የተጀመረው በዜሮ ባጀት ነው፡፡ ፈረንጆቹም ሆኑ
ሌሎች በማይረዱበት ሁኔታ እንደዚህ ብዙ ዓመት የሚፈጅ ትልቅ ነገር መጀመር ላይ ጥያቄ አለኝ፡፡ ያዋጣል ወይ?
ምናልባት መንግሥት ብር አትሜ እሠራዋለሁ ሊል ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ የራሱ የሆነ ችግር አለው፡፡ ኢንፍሌሽን
ያመጣል፤ የኑሮ ውድነትን ያባብሳል፡፡
በሌላ በኩልም ለምን ኢህአዴግ ግድቡን በግብጽ አፍንጫ ስር መስራት
ፈለገ? የሚል የጂኦግራፊ ጥያቄም አለኝ፡፡ የግብጽ አፍንጫ ማለቴ ሱዳንን ነው፡፡ ለምን ኢህአዴግ ግድቡን እንደዚህ
ወደ ሱዳን አቅርቦ መስራት ፈለገ? ይሄንን የምለው ግብጽ በቀላሉ ሊያጠቃን ይችላል ብዬ ስለማስብ ነው፡፡ የግብጽን
ልብ ሙሉ ለሙሉ ማወቅ ስለማይቻል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግ ነበር፡፡ ምን ያህል ስለ ቦታው ተጠንቷል የሚለው ለእኔ
ጥያቄ ነው፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- እዚህ ላይ
ላቋርጥዎትና ምናልባት እርስዎ ቦታውን ሄደው አይተውት ሊሆን ይችላል፡፡ እኔም በአጋጣሚ የማየቱ ዕድል ነበረኝ፡፡
እናም ተፈጥሮ ለግድብ ግንባታ በአባይ ተፋሰስ ላይ ከሰጠቻቸው ቦታዎች ሁሉ በጣም ምቹ የሆነው አሁን ግድቡ
የሚሠራበት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ዶክተር መረራ፡- የሚሉ አሉ፡፡ ነገር
ግን ለመስኖ መጠቀም አንችልም፡፡ ግድብ ስትገነባ ለኃይልም ብቻ ሳይሆን ለመስኖም ማዋል አለብህ፡፡ ስለዚህ ይሄንን
ግድብ እዚያ ላይ ከመስራት ይልቅ የአባይ ገባር የሆኑ ትልልቅ ወንዞችን ተጠቅመህ ስድስትና ሰባት ግድቦችን መስራት
ይቻል ነበር፡፡ ግብጾችንም ብዙ ሳታስደነግጣቸው ለኃይልም ለመስኖም መጠቀም ይቻል ነበር፡፡
ስድስት ሺ ሜጋ ዋት በአንዴ ከማመንጨት አንድ አንድ ሺ የሚያመነጩ ሌሎች ግድቦችን በጊዜ ሂደት መስራት ይሻል ነበር፡፡ ይሄ ግድብ አሁን ባለው የሥራ ሂደት አስር ዓመት መፍጀቱ አይቀርም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ዶክተር የተፋሰሱ የታችኛው አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሚያመነጭ ግድብ ይሄንን ያህል ከጮኹ ጭራሽ የመስኖ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ቢሰራ ዝም የሚሉ ይመስልዎታል?
ዶክተር መረራ፡- እነርሱን ሳታደናግጥ እንደ ጉደርና ደዴሳ ያሉ የአባይ ገባር ወንዞችን በመጠቀም እንዳትሰራ ግብጽ በየቦታው እየዞረች የምታስተጓጉልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- በትክክል የሚሉት
ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ ተከዜ ላይ 300 ሜጋ ዋት ጣና በለስ ላይም 470 ሜጋዋት የሚያመነጩ የኤሌክትሪክ ኃይል
ማመንጫዎች ተሠርተዋል፡፡ነገር ግን ለእነዚህ ፕሮጀክቶች ብድርም ሆነ እርዳታ ማግኘት ስላልተቻለ በራስ ወጪ የተሠሩ
ናቸው፡፡ ይሄንን እርስዎ ካሉኝ ጋር እንዴት ያዩታል?
ዶክተር መረራ፡- ግብጽና የአባይ ውሃ እንዲሁ በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡ እናሳምናለን ምናምን የሚባለው ነገር ለእኔ ቀላል አይመስለኝም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ስለዚህ ግብጾች የሚያነሱት ጥያቄ ትክክል ነው እያሉኝ ነው?
ዶክተር መረራ፡- ትክክል ነው አላልኩም፡፡ መጠቀሙ የኢትዮጵያ ሕዝብ መብት ነው፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ታዲያ ጥያቄዎ ምንድን ነው?
ዶክተር መረራ፡- ጥያቄው ስትራቴጂው
ላይ ነው፡፡ ሁሉንም ሀብትህን ሰብስበህ አንድ ግድብ ላይ ማዋሉ፣ የግድቡ መገንቢያ ቦታ ተገቢነትና ሌሎች ተያያዥ
ጉዳዮች ጥያቄዎች ናቸው፡፡ አንድ ትልቅ ባለሥልጣን ከእንቅልፉ ሲነቃ እንዲህ ዓይነት ትልቅ ፕሮጀክት መስራት አለብኝ
ካለ ችግር ነው፡፡ በነገራችን ላይ በሌሎች አገሮች ላይ ትልልቅ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥያቄ አለባቸው፡፡
የግብጾችን ጉዳይ በተመለከተ አንዳንድ ነገሮችን ብነግርህ ላትረዳው
ትችላለህ፡፡ እኔ ግብጽ ስለነበርኩ አውቀዋለሁ፡፡ ለእኔ ምክንያታዊ የሆኑ ላንተ ጨርሶ የማይገቡህ ነገሮች ሁሉ
አሉ፡፡ አባይ ለግብጾች ሁሉ ነገራቸው ነው፡፡ ትራንስፖርት ብትል ምግብ፣ ውሃው ቤታቸው ሁሉ አባይ ነው፡፡
ፍቅራቸው፣ ዘፈናቸው ፊልማቸው ሁሉ አባይ ነው፡፡ ቤት ኪራይ መከራየት ከፈለክ እንኳን የቤቱ መስኮት ወደ አባይ
ወንዝ የዞረ ከሆነ ኪራዩ እጥፍ ነው፡፡ በቃ የግብጾች ሕይወት አባይ ነው ብልህ ይቀላል፡፡ ስለዚህ ግብጽን አይዞህ
ምንም አትሆንም ብትለው በቀላሉ አይቀበልህም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ጥሩ፤ የተፋሰሱ አገራት በጋራ ለመልማት እንዲችሉ መደረግ ያለበት ምንድንነው ይላሉ? ወይንም እርስዎ ቢሆኑ ምን ያደርጋሉ?
ዶክተር መረራ፡- እኔ ብሆን ኖሮ ቅድም
ያልኳቸውን ነገሮች አደርጋለሁ፡፡ በአቅማችን የሚሠሩ፤ ከውጭም እርዳታ የማገኝባቸውን ትናንሽ አባዮችን እገነባ
ነበር፡፡ አስር ዓመት አንድ ግድብ ከመገንባት በየዓመቱ አንድ ሺ ሜጋ ዋት የሚያመነጩ ግድቦችን መስራት
እመርጣለሁ፡፡ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰባት አባዮችን መስራት የሚያስችል ፖሊሲም ነበር የምከተለው፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- የሚቻል ይመስልዎታል
ዶክተር? ለምሳሌ እንዳልኩዎት ተከዜ ላይም ሆነ ጣና በለስ ላይ እንዲሁም ግቤ ሦስተኛ ላይ እርስዎ የሚሉት
ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን በግብጾች ምክንያት ምንም ዓይነት ብድርም ሆነ እርዳታ ማግኘት እንዳልተቻለ መንግሥት በወቅቱ
አስታውቋል፡፡ ስለዚህ እርስዎ የሚሉት አማራጭ የሚቻል ይመስልዎታል?
ዶክተር መረራ፡-እነርሱማ አንተ አቅም
እስከሌለህ ድረስ ጎረቤትህ አንተን የማይገፋበት ምክንያት የለም፡፡ ነገር ግን ጎረቤትህ ያለ የሌለ ዱላውን ሰብስቦ
ድበደባ ውስጥ ከሚገባብህ ቀስ እያልክ አቅምህንም እየገነባህ መጓዝ ትችላለህ፡፡ በእዚህ መንገድ ከተጓዝክ ያ
ጎረቤትህ ከአንተ ጋር ከመደራደር ውጪ ምንም አማራጭ አይኖረውም፡፡
ለምሳሌ የግብጽ ፕሬዚዳንት ከፖለቲከኞች ጋር ያደረጉት ውይይት
በቀጥታ ቴሌቪዥን የተላለፈው በስህተት ነው ብለዋል፡፡ እኔ ግን ስህተት በሚለው አልስማማበትም፡፡ ሆን ብለው
ያደረጉት ነው፡፡ ለማንኛውም ኢትዮጵያ በኤርትራ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌም ሆነ በኦሮሞ በኩል ያልተመለሱ ጥያቄዎች ስላሉ
እና ብሔራዊ መግባባትም ስላልተፈጠረ ግብጾች በእነዚህ ቀዳዳዎች ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ዙሪያ ማሰብ
ያስፈልጋል፡፡
የግብጽን አጀንዳ የያዙ ሌሎች አገራትም አሉ፡፡ የመጀመሪያው
የሳውዲአረቢያ መከላከያ ሚኒስትር ነው፡፡ ግብጾች በአረቡ ዓለም ተሰሚነት ስላላቸው የአፍሪካን ጨምሮ ሌሎች እንደ
ሳውዲ ያሉ አረብ አገራትን ልታንቀሳቅስና ኢትዮጵያ ግድቡን እያለመች እንድትኖር ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ግብጽ
ተስማምቻለሁ እሺ እያለች ሌሎች ሥራዎችንም ልትሠራ ትችላለች፡፡ ለወደፊቱ ይጠና የሚለውም የራሱ ሌላ መዘዝ አለው፡፡
ምክንያቱም ጊዜ ለመግዛት የሚፈጥሩት አማራጭ ነውና፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡-እርስዎም እንዳሉት
ግብጾችም በቀጥታ በስህተት ተላለፈ ባሉት የቴሌቪዥን ስርጭት ላይ እንደተደመጠው እንጠቀም ካሏቸው አማራጮች መካከል
ተቃዋሚዎችን በመደገፍ መንግሥትን እናዳክም የሚለው አንዱ ነው፡፡ ለእኔ እንደሚገባኝ ደግሞ ተቃዋሚ ሲባል በውጭ
ያለው ብቻ አይመስለኝም፤ እናንተንም ይጨምራል፡፡ ለመሆኑ ይሄ ጥያቄ ከግብጽ ቢቀርብላችሁ ምላሻችሁ ምንድንነው፣
ዶክተር መረራ፡- ይሄንን በተመለከተ
እኛ እንደ መድረክ መግለጫ ሰጥተንበታል፡፡ ኢትዮጵያ ሀብቷን መጠቀም ብሔራዊ መብቷ ነው፡፡ በሀገር ውስጥም ሆነ
በውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች ግብጽ ወደ ምትለው ጉዳይ ውስጥ ላይገቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁሉም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ
ኃይሎች ከግብጽ ጋር አይተባበሩም ብለህ ደርቀህ መከራከር አትችልም፡፡«ከአባይ በፊት የመብት ጥሰት ይገደብ» የሚሉ
አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች በተወሰነ መልኩ ከግብጽ ጋር አይተባበሩም ብለህ የጅል ክርክር መከራከርም አይኖርብህም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- እርስዎ እንደ ተቀዋሚም ሆነ እንደ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ከግብጽ ጋር ሊተባበሩ ይችላሉ ብለው ለሚጠረጥሯቸው ኃይሎች ምን ዓይነት ምላሽ አለዎት?
ዶክተር መረራ፡- አታድርጉ ልትል
ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ላይቀበሉህ ይችላሉ፡፡ እነርሱ የተለያየ ነገር ያነሳሉ፡፡ ለምሳሌ ከኤርትራ መንግሥት ጋር
የተለያየ ትብብር ያላቸው ኃይሎቸ አሉ፡፡ እነዚህን ኃይሎች ምንም ብትላቸው አይሰሙህም፡፡ እነርሱ «ከኢህአዴግ ያነሰ
የሀገር ፍቅር የለንም» ይላሉ፡፡ ስለዚህ ክርክሩ ውስጥ ብትገባም በቀላሉ ልታሳምናቸው አትችልም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- እንደ ተቃዋሚ
ፖለቲካ ፓርቲም ሊሆን ይችላል እንደ ተራ ኢትዮጵያዊ ወይንም ዜጋ ከግብጽ የምንማረው ነገር አለ፡፡ ግብጾች የቱንም
ያህል መንግሥታቸውን አምርረው ቢጠሉ በሀገር ጉዳይ ግን ምንጊዜም አንድ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ በዓባይ ላይ ያላቸው
አቋም የተለየ ነው፡፡ ይሄንንም በቀጥታ ከተላለፈው የቴሌቪዥናቸው ስርጭት መረዳት እንችላለን፡፡ ወዲህ ወደ እኛ
ሀገር ስንመለስ ግን በአባይ ላይ እንኳን አንድ መሆን አልቻልንም፡፡ በእዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት?
ዶክተር መረራ፡- እኔ ከምንም በላይ
የምለው ኳሱ ያለው በኢህአዴግ ሜዳ ላይ ነው፡፡ በኢጣሊያ ዘመን ያየነው ነገር ነው፡፡ በእዚያ ዘመን የኢጣሊያን
ባንዳ ሆነው ፔሮል ላይ ሳይቀር የሰፈሩና ያገለገሉ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኃይለሥላሴ ሌላ
ኢትዮጵያ ሌላ ብለው ከእሥር ቤት ወጥተው የተዋጉ እንደ ባልቻ አባነፍሶ ያሉ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ከእዚህ
የምንማረው ምንድን ነው፣ መንግሥት ስትሆን ቀዳዳ እንዳይከፈት ማድረግ አለብህ፡፡ በሀገር ፖለቲካ ላይ ብሔራዊ
መግባባት ካልፈጠርክ ግብጾች ነገም ሆነ ከነገ ወዲያ የውጭን ኃይል ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡
ላለፉት 150 ዓመታት ያለውን የኢትዮጵያን ታሪክ ስናየው ደግሞ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከውጭ እጅ ነፃ የሆነ አይደለም፡፡ ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ አሁን እስካለው የኢህአዴግ መንግሥት
ድረስ ያለው እውነታ የሚያስረዳው ይሄንን ነው፡፡
መንግሥት በሀገር ጉዳይ ላይ ተቃዋሚዎችን በሙሉ ልብ እንዲሳተፉ
ካላደረገ ከእኔ ጋር አልተሳተፉም ብሎ ጧትና ማታ መጮሁ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ተቃዋሚውም በማይሆን መንገድ በሀገር
ጉዳይ ላይ መደራደር የለበትም፤ ይሄ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲል ብሔራዊ
ጥቅም የሚጎዳ ነገር መፈጸም የለበትም፡፡ ስለዚህ በሁለቱም ወገን ጉዳዩ መታያት አለበት፡፡ ኢህአዴግ በሀገር ጉዳይ
ላይ ከተቃዋሚዎች ጋር ብሔራዊ መግባባት መፍጠርና ወደ ውጪ እንዳያዩ ማድረግ ካልቻለ ዋናው ጥፋተኛ መንግሥት ነው
የሚሆነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው ክርክር የሚያስኬድ አይደለም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- በእዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ መንግሥት በአባይ ዙሪያ ምን ማድረግ አለበት ነው የሚሉት?
ዶክተር መረራ፡- እኔ አሁን ኢህአዴግ በገባበት ደረጃ የተሻለውን የሚያውቀው እራሱ ኢህአዴግ ብቻ ነው።
ዓርዓያ ጌታቸው፡- በዲፕሎማሲው ይቀጥል ማለትዎ ነው?
ዶክተር መረራ፡- ይሄ ምንም ጥርጥር
የለውም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው ለዲፕሎማሲ ነው፡፡ በእኔ እይታ ጉዳዩን ስመለከተው ግብጾች ጦርነት ውስጥ ይገባሉ የሚል
እምነት የለኝም፡፡ ሌሎች ብዙ አማራጮች አሏቸው፡፡ ግድቡ ተሰርቶ እንዳያልቅ ሊያደርጉ የሚያስችሉ የተሻሉ መንገዶች
አሏቸው፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ለምሳሌ እንዴት ዓይነት?
ዶክተር መረራ፡- ቀዳዳዎችን በመጠቀም
ሊሆን ይችላል፡፡ ሶማሊያ አለች፤ ለአልሸባብ የፈለጉትን ማቀበልም አለ፤ ጂቡቲንም ማባበል ይኖራል፤ እኔ እዚህ ጨዋታ
ውስጥ አትገባም ብዬ የማስበው ኬንያን ብቻ ነው፡፡ እርሷም ብትሆን አንዳንድ ጊዜ አይታ እንዳላየች የምትሆነው
ነገር አላት፡፡
ስለዚህ የዲፕሎማሲው መንገድ ካልሰራላት ግብፅ የምትከተለው መንገድ
ይሄ ነው የሚሆነው፡፡ ግድቡ እዚያ አይደርስም እንጂ ተሰርቶ ካለቀ ግን የግድቡን ደህንነት የምትጠብቀው እራሷ
ግብፅ ነው የምትሆነው፡፡ ምክንያቱም ግድቡ አንድ ነገር ከሆነ ውሃው ጠራርጎ ይዞ የሚሄደው ግብፅን እንጂ ኢትዮጵያን
አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያም በዲፕሎ ማሲው መግፋት እንዳለ ሆኖ እስከዚያው ራሷን ማደራጀት አለባት፡፡
ግብፅ ሠራዊቷን ልካ ኢትዮጵያን ትወራለች የሚል እምነት የለኝም፡፡
ከእዚያ ይልቅ መንግሥትን ሊያዳክሙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭንም ብቻ ሳይሆን የውስጡንም የቤት
ሥራ መስራት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ እየተራበ ግብፅ የተሻለ እየተመገበች መቀጠል አይኖርብንም፡፡ በመሆኑም
የራስህን ጥቅም አሳልፈህ በማይሰጥ መልኩ መደራደር ያስፈልጋል፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ለመጨረሻ ጊዜ ልጠይቅዎት፡፡ በእርስዎ ግምት የግድቡ ግንባታ ይሳካል ብለው ያምናሉ? እርስዎስ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊም ሆነ የመንግሥት ሠራተኛ ለግደቡ ቦንድ ገዝተዋል?
ዶክተር መረራ፡- ግድቡ ያልቃል የሚለው
ላይ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ምክንያቱም በዜሮ ባጀት እየተሠራ ያለ ፕሮጀከት ነውና፡፡ እስካሁን የተሰበሰበው ብርም ከ10
በመቶ በላይ ሊሆን አልቻለም፡፡ ስለዚህ የሀገሪቷን ሀብትና ባጀት ሁሉ ወደ ፕሮጀከቱ ማዞር ነው ያለው አማራጭ፡፡
ይሄ ደግሞ የራሱ ችግር አለው፡፡ ስለዚህ በቀላሉ ያልቃል ብዬ አላምንም፡፡ የውጭ ጣጣ ሲጨመርበት ደግሞ ችግሩ
በዚያው ልክ ይጨምራል፡፡ የቦንድ ግዥን በተመለከተ ወደድንም ጠላንም ዩኒቨርሲቲው የአንድ ወር ደመወዛችንን በዓመት
ተከፍሎ የሚያልቅ ብሎ ወስዷል፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- እርስዎ ተስማምተዋል?
ዶክተር መረራ፡- እኔ በእውነቱ አልተጠየኩም፤ በግድ ነው የተወሰደብኝ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ሦስት አራት ሰው አነጋግሮ ሠራተኛው ወስኗል ማለቱ አግባብ አይደለም፡፡ ይሄንንም በግልጽ በደብዳቤ ጋዜጣ ላይ የጻፉ አሉ፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ወደ እርስዎ ልመለስና፣ እርስዎ ቢሮዎ ለግድቡ አስተዋፅኦ ያድርጉ የሚል ደብዳቤ ወይንም ቅጽ ቢመጣልዎት ይፈርማሉ?
ዶክተር መረራ፡- እርሱን እንኳ ያን ጊዜ ምን እንደማደርግ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ነገር ግን በፈቃደኝነት ፈርሙ ቢባል ብዙ ሰው አይፈርምም የሚል እምነት አለኝ፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ጥሩ መንግሥት
ተከዜን በአራት ቢሊዮን ብር፣ ጣና በለስን በሰባት ቢሊዮን ብር በራሱ ወጪ ሰርቶ አሳይቷል፡፡ አሁንም ጊቤ ሦስተኛን
በራሱ ወጪ እያሠራ ነው፡፡ እንደው እነዚህን ነገሮች ሲመለከቱ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሰርቶ ይጨርሰዋል
የሚል ጥርጣሬ አያጭርብዎትም?
ዶክተር መረራ፡- ሁለቱ ግድቦች
የነበረባቸው ችግር የገንዘብ ብቻ ነው፡፡ ይሄ ግድብ ግን ችግሩ የገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ የውጭ አይኖች ሁሉ
ኢትዮጵያ ላይ እንዲሆን ያደረገ ፕሮጀክት ነው፡፡ የአረቡ ዓለምንም በኢትዮጵያ ላይ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ከውስጥም
ከውጭም በቂ ድጋፍ ሳይኖርህ ጠንከር ያለ የውጭ ዓለምም ተቃውሞ እየገጠመህ በቀላሉ የምታሳካው ፕሮጀክት አይደለም፡፡
ግድቡ እስኪያልቅ ድረስ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ሁሉ ልታጥፍ፣ ግሽበት ውስጥ ሁሉ ልትገባ ትችላለህ፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- እስኪ ወደ ሌላ
ሃሳብ ልውሰድዎት፡፡ ግብጾች በተደጋጋሚ የሚያነሷ ቸው የ1929 እና የ1959 ስምምነቶችን ነው፡፡ አሁን ደግሞ
የተፋሰሱ የላይኛው አገሮች የተፈራረሙት የኢንቴቤው ስምምነት አለ፡፡ እነዚህን ስምምነቶች እንዴት ያዩዋቸዋል?
ዶክተር መረራ፡- ይሄ ምንም
የሚያነጋግር ነገር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ላልፈረመችበት ሕግ የምትገደድበት ምክንያት የለም፡፡ ያ የቅኝ ግዛት ሕግ
መቀየር አለበት፡፡ 86 በመቶ የሚያመነጭ አገር እንዴት አንድ ሊትር ውሃ እንኳን አይሰጠውም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- እርስዎ እንደ ግለሰብ ወይንም በፓርቲዎ ደረጃ መንግሥት ቢሆኑ ቅድሚያ የሚሰጧቸው ፕሮጀክቶች ምን ምን ይሆናሉ?
ዶክተር መረራ፡- እኔ ለምግብ ዋስትና ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡ በእዚህ ላይ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ይሄስ ቀላል የሚሆን ይመስልዎታል፣ ግብጾችስ ዝም የሚሉ ይመስልዎታል?
ዶክተር መረራ፡- አልኩህ እኮ ግብጾች
ሊቃወሙ ይችላሉ፡፡ ትንንሽ ፕሮጀክቶችን እየተጠቀምክ ግን አቅምህን ታዳብራለህ፡፡ በመጨረሻ ይጠቅማል ከተባለ ከ30
ወይንም ከ40 ዓመት በኋላ ወደ አባይ ልትሄድ ትችላለህ፡፡ ያን ጊዜ ግብጾችም ሊያግዙህ ይችላሉ፡፡ ግብጾችም ብዙ
ውሃ እንዲመነጭ የኢትዮጵያን ደን በማልማት በኩል እንዲገቡ አደርጋለሁ፡፡ እነርሱ ዛሬ የሚያስቡት ኢትዮጵያን ማልማት
ሳይሆን ውሃውን ወደ ሲና በረሃ አሻግረው ለእስራኤል መስጠትን ነው፡፡
ሌላው ኢህአዴግ ለሚለው የገጠር ልማትና ኢንዱስትሪ ቅድሚያ
እሰጣለሁ፡፡ ኢህአዴግ እኮ ዝም ብሎ ይጮሃል እንጂ በገጠር ልማት ላይ አልሠራም፡፡ ገና ብዙ ሥራዎች ገበሬው ላይ
አልተሰሩም፡፡ አሁንም ድረስ ገበሬው የሚጠቀመው የ13ኛው ክፍለ ዘመን አስተራረስን ነው፡፡ ይሄንን ካልቀየርክ ለውጥ
አታመጣም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ግን እኮ ዶክተር ምርታማነት ጨምሯል?
ዶክተር መረራ፡- ይሄንን እኮ ኢህአዴግ
በባህርዳሩ ጉባኤው አምኗል፡፡ ካድሬው ለምቷል፡፡ ገበሬው ግን ገና ነው፡፡ በሚፈለገው መጠን አልለማም፡፡ ስለዚህ
ለመስኖ ትኩረት መስጠትና የግብርና አብዮት ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው የኢንዱስትሪ ጥያቄ መምጣት
ያለበት፡፡ የኢንዱስትሪ አብዮት ካላመጣህ ደግሞ ኢትዮጵያን የትም ማድረስ አትችልም፡፡
ዓርዓያ ጌታቸው፡- ዶክተር ለሰጡኝ ማብራሪያ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ መጥቼ አስተያየትዎን እወስድ ይሆናል…
ዶክተር መረራ፡- (ከረጅም ሳቅ በኋላ) ምንም ችግር የለውም፡፡ ለእዚያ ያብቃን፡፡ ያን ጊዜ መወቃቀስም መሞጋገስም ይቻላል፡፡
ref... danielberhane.com
No comments:
Post a Comment